ኢትዮጵያ በአባይ ተፋሰስ ዙሪያ ያከናወነቻቸው ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራዎች የተፋሰሱን ሀገራት ከግብፅ ነጥላ ከጎኗ እንድታሰልፍ አስችሏታል-ምሁራን
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በአባይ ተፋሰስ ዙሪያ ያከናወነቻቸው ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራዎች የተፋሰሱን ሀገራት ከግብፅ ነጥላ ከጎኗ እንድታሰልፍ ማስቻሉን የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን ገለጹ።
ድርድሩ የምትፈልገውን ያላመጣላት ካይሮ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ እየነገረች ያለችው ሀሰት መሆኑን ለማሳወቅም ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲ ስራ መጠመድ እንዳለባት ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉ ምሁራን ተናግረዋል።
በድርድሩ ሂደት ሰፊ ተሳትፎ ያደረጉትና በግብፅ የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት አምባሳደር ኢብራጂም ኢድሪስ፥ኢትዮጵያ በፍትሃዊ ተጠቃሚነት ላይ በተመሰረተው ዲፕሎማሲዋ ወዳጇን ስታበዛ፤ በህገመንግስቷ ጭምር አባይ የኔ ነው የምትለው ግብፅ ደግሞ የተፋሰሱ ሀገራት እየገፏት ነው ብለዋል።
ግብፅ ከጥንትም አባይን ስታነሳ የውሃ ጉዳይ ብቻ አድርጋ አይደለም፤ አባይ ሲነካ ብሄራዊ ደህንነቴ ይቃወሳል የሚል ስጋቷን ነው ደጋግማ የምታቀርበው።
የሀገሪቱ መሪዎችም በአባይ ዙሪያ ወጥ አቋም እንዳላቸው ይነገራል።
ከዲፕሎማሲ ይልቅም 95 በመቶ የቃላት ጦርነት በመክፈት ላይ የሚጠመዱት መሪዎቿ፥ በውሃው ባለቤት ኢትዮጵያ ላይ ዘርፈ ብዙ ጫናዎችን ሲያደርጉ ዘመናት አልፈዋል፤ አሁንም ቀጥለውበታል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና አለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ ዶክተር ደመቀ ሀጪሶም፥ኢትዮጵያ የሁለትዮሽ እና ባለብዙ ወገን ድጋፍ እንዳታገኝ ካይሮ በርካታ ዲፕሎማሲያዊ ስራዎች ማከናወኗን ያነሳሉ።
ግብፅ በአፍሪካ ህብረትም ሆነ በመንግስታቱ ድርጅት ውድቅ የተደረጉ የቅኝ ግዛት ስምምነቶችን እየጠቀሰች የአባይ ውሃን በብቸኝነት የመጠቀም ፍላጎቷን ነው ስታንጸባርቅ የቆየችው።
ኢትዮጵያ በበኩሏ አባይ የሁላችንም ነው፤ ኢትዮጵያም፣ግብፅም ሌሎች የተፋሰሱ ሀገራትም በጋራ ብንጠቀምበት ይበቃናል የሚል አቋሟን ስታንፀባርቅ ቆይታለች።
በ2010 ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር ስምምነት ላይ እንዲደረስም ይሄው በጋራ እንጠቀምበት የሚለው አቋሟ ከፍ ያለ ሚና እንደነበረው ነው ዶክተር ደመቀ የሚያነሱት።
የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የድንበርና ድንበር ተሻጋሪ ሀብቶች አማካሪ አምባሳደር ኢብራሂም ኢድሪስ በበኩላቸው ፥ባለፉት 19 ዓመታት የኢትዮጵያ የድርድር ቡድን አባል እንደመሆናቸው፤ ኢትዮጵያ በአባይ ጉዳይ የገጠሟትን ፈተናዎች እና ስኬቶች በደንብ ያውቁታል።
አምባሳደር ኢብራሂም እንደሚሉት ብቸኛ የነበረችው ኢትዮጵያ፤ በውጤታማ የዲፕሎማሲ ስራ ግብፅ እና ሱዳን ብቻቸውን እንዲቀሩ አድርጋለች።
የተፋሰሱ ሀገራት እንደ አውሮፓውያኑ በ2010 በሻርም አልሸክ ባደረጉት ስብሰባ አብዛኞቹ ከኢትዮጵያ ጎን ተሰልፈዋል፤ ግብፅ እና ሱዳንም በሌላኛው ወገን።
በ2011 በኡጋንዳ ኢንቴቤ በተደረሰው ስምምነትም ስድስት ሀገራት ፈርመው እስካሁን አራት ሀገራት አፅድቀውታል።
ኢትዮጵያ የታላቁ ህዳሴ ግድብን መገንባት ከጀመረች በኋላ ሱዳንን ጨምሮ አብዛኞቹን የተፋሰሱ ሀገራት ከጎኗ ማሰለፍ መቻሏን ነው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ ዶክተር ደመቀ ሀጪሶ ያነሱት።
በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ አቶ እንዳለ ንጉሴም፥ ኢትዮጵያ ለተፋሰሱ ሀገራት ስለግድቡ ግልፅነት ለመፍጠር ያደረገችው ጥረት ስኬታማ የነበረ ቢሆንም፤ ግብጾቸ ግን አሁንም ድረስ አባይ የኢትዮጵያ ነው ብለው አያምኑም።
ኢትዮጵያ በአባይ ዙሪያ ስኬታማ ዲፕሎማሲያዊ ስራ አከናውናለች፤በግድቡ ዙሪያም አለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን እንዲያጠና ከማድረግ ጀምሮ ለረጅም አመታት ድርድሮች ተደርገዋል።
የሀገራቱ ሚኒስትሮች ግድቡን እንዲጎበኙ በመፍቀድም ግልፀኝነቷን ማሳየቷም አኤዘነጋም።
አምባሳደር ኢብራሂም ምላሽ ገለጻ ግብፅ ከዋሽንግተኑ ድርድር በኋላ በአሜሪካ እና አለም ባንክ በኩል ጫና ለማሳደር ከመሞከር ባለፈ ለተለያዩ ሀገራትም ዲፕሎማሲያዊ ጫና ለመፍጠር እየሰራች ነው።
በአንጻሩ ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ስምምነቶች አግልላችሁኛል ጥቅሜንና ሉአላዊነቴን የሚፃረር ስምምነቶች ፈርማችኋል ብላ ግብፅ እና ሱዳንን ችላ አላለቻቸውም።
በግድቡ ግንባታ ድንቡሎ ሳንቲም ያላበደሩት የአለም ባንክ እና አሜሪካ ታዛቢ ሆነን እንምጣ ሲሉም የሰለጠነ ዲፕሎማሲ እንደሚያራምድ ሀገር ፈቅዳለች።
የግብፅ ተለዋዋጭ ባህሪ ግን የዋሽንግተኑ ድርድር ፍሬ ሳያፈራ ኢትዮጵያ አዲስ ስምምነት በማርቀቅ ላይ ናት።
በርግጥ ኢትዮጵያ ከእስካሁኑ አካሄዷ ምን ትማራለች፤ ኢትዮጵያውያንስ እንዴት ወደ መልካም እድል አንቀይረው ለፖለቲካ ሳይንስ ምሁራኑ ያቀረብኩት ጥያቄ ነው።
ምሁራኑ ግብፅ በጉንደት እና ጉራ የገጠማትን ሽንፈት ዘንግታ፤ በተደጋጋሚ የጦርነት ነጋሪት ብትጎስምም፤ ኢትዮጵያ በኩራት ተሞልታ አባይ የኛ ብቻ ኑ እና እንግጠም ብላ እንደማታውቅ ይናገራሉ።
የካይሮ የብቸኛ ባለቤትነት እና ጥቅሜን አትጋሩኝ ሀሳብ ግን የተሸነፈ ሀሳብ መሆኑን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን 71 በመቶ በማድረስ እያሳየች ነው።
ድርድሩ የምትፈልገውን ያላመጣላት ካይሮ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ እየነገረች ያለችው ሀሰት መሆኑን ለማሳወቅም ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲ ስራ መጠመድ እንዳለባት ምሁራን አሳስበዋል።
በፋሲካው ታደሰ