የዩክሬንን እህል የጫነች የመጀመሪያዋ መርከብ ከኦዴሳ ወደብ ተንቀሳቀሰች
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከሩሲያ ጋር በተደረሰው ሥምምነት መሠረት የመጀመሪያውን የእህል ወጪ ንግድ የጫነች መርከብ ዩክሬንን ለቃ መውጣቷን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ዛሬ የቱርክ እና የዩክሬን ባለሥልጣናት እንዳስታወቁት እህል የጫነችው መርከብ የኦዴሳን ደቡባዊ ወደብ ለቃ ጉዞ ማድረግ ጀምራለች፡፡
መርከቧ 26 ሺህ ቶን በቆሎ ጭና መንቀሳቀሷም ነው የተሰማው።
የእህል ወጪ ንግዱ በሥምምነቱ መሠረት ዳግም መጀመር የዓለም አቀፉን የምግብ እጥረት ያቃልላል የምግብ ዋጋም እንዲቀንስ ያደርጋል ተብሎ ተሥፋ ተጥሎበታል፡፡
ከመርከቧ መንቀሳቀስ ቀደም ብሎ ቱርክ በሰጠችው መግለጫ መሰረት፥ በ”ሴራሊዮን ሰንደቅ ዓላማ” የምትንቀሳቀሰው መርከብ መዳረሻዋ ሊባኖስ ወደብ ነው፡፡
የእህል ምርቱን በመርከብ የማጓጓዝ ሥራው በመጪዎቹ ሣምንታት እንደሚቀጥልም ነው ቱርክ ያስታወቀችው።
የዩክሬን መሰረተ ልማት ሚኒስትር አሌክሳንደር ኩብረኮቭ እንደተናገሩት፥ ሀገራቸው ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በዓለም ላይ የተከሰተውን የእህል ምርት አቅርቦት ችግር ለማቃለል የበኩሏን ጥረት ታደርጋለች።
ሌሎች 16 መርከቦች ከኦዴሳ ግዛት በመጪዎቹ ሣምንታት ውስጥ እንደሚንቀሳቀሱም ነው ሚኒስትሩ ያስታወቁት።