Fana: At a Speed of Life!

የአፋር ክልል ምክር ቤት ለ2015 ዓ/ም ከ10 ቢሊየን ብር በላይ በጀት አጸደቀ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፋር ክልል ምክር ቤት ለ2015 በጀት አመት 10 ቢሊየን 132 ሚሊየን 869 ሺህ 117 ብር በጀት አጽድቋል።

ለከታታይ ቀናት በቀጠለዉ 6ኛዉ የክልሉ ምክር ቤት 1ኛ አመት የስራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባኤ የአስፈጻሚ አካላት ምክርቤቱ አፈጻጸምን ጨምሮ የጠቅላይ ፍርድ ቤትንና የክልሉ ዋና ኦዲተር የስራ አፈጻጸም ላይ ዉይይት በማድረግ ሪፖርቶቹን በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።

በምክር ቤቱ የዛሬ ውሎ የክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ አህመድ መሀመድ ረቂቅ በጀቱን ለምክር ቤቱ በዝርዝር ሲያቀርቡ በጀቱ ለተለያዩ የማህበራዊና ኢኮኖሚያ መሠረተ-ልማቶች ማስፋፊያ እንደሚውል ገልጸዋል።

የበጀቱ ምንጭ ከክልሉ ገቢና ከፌዴራል መንግስት የድጎማ ቀመርና ከውጭ እርዳታ የሚገኝ መሆኑን አብራርተዋል።

በጀቱ ለድህነት ቅነሳ ጉልህ አስተዋጽኦ ለሚኖራቸዉና ህብረተሰቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ሊመልሱ ለሚችሉ የልማት ስራዎች እንደሚውልም ተናግረዋል።

በቀረበዉ ረቂቅ በጀት ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጡት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ በበኩላቸዉ÷ በጀቱ በዋናነት ተጀምረዉ ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት በማድረግ መደልደሉን ገልጸዋል።

የክልሉን የልማት ፍላጎት ለማሟላት ገቢ የማሰባሰብ አቅምን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አስገንዝበው፤ በዚህ ረገድ ጠንካራ ዕቅድ በማውጣት በየደረጃዉ የሚገኙ አመራሮች ቀዳሚ ተግባራቸው አድርገው እንዲሰሩበት አሳስበዋል።

በተጨማሪ አላስፈላጊ ወጪዎችን በመቀነስ ህዝቡን በማስተባበርና የተፈጥሮ ጸጋዎችን በአግባቡ በማልማት የህዝቡን ኑሮ ለማሻሻል አመራሩ እንዲሰራ አቅጣጫ አስቀምጠናል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.