Fana: At a Speed of Life!

ዑመድ ዑኩሪ የኦማኑን ክለብ ተቀላቀለ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያዊው አጥቂ ዑመድ ዑኩሪ የኦማኑን ክለብ አል-ሱዋይክ መቀላቀሉ ተገለጸ፡፡

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለመከላከያ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ በመጫወት ከሀገራችን የስፖርት ማህበረሰብ ጋር መተዋወቅ የቻለው ባለ ግራ እግሩ አጥቂ÷ 2006 ላይ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ እና ኮከብ ተጫዋች በመሆን ከፈፀመ በኋላ ወደ ግብፅ ሊግ ማምራቱ ይታወሳል።
በዚያም ለአል-ኢትሀድ አሌክሳንድሪያ፣ ኤንፒ፣ ኤል ኢታንግ አል አርቢ፣ ሶሞሀ እና አስዋን ክለቦች ስድስት ዓመት ከግማሽ ያህሉን በማሳለፍ፥ በ2013 አጋማሽ ወደ ሀገሩ በመመለስ በሀድያ ሆሳዕና መለያ ለአንድ ዓመት ከግማሽ በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በመጫወት ቆይታን አድርጓል፡፡

ተጫዋቹ ከሀድያ ሆሰዕና ጋር ከሳምንታት በፊት ለመቀጠል ድርድር ማድረግ ቢችልም ስምምነት ላይ መድረስ ባለመቻላቸው ወደ ግብፅ አምርቶ ለቀድሞው ክለቡ ሶሞሀ ለመጫወት ስለመቃረቡ ሲገለፅ ቆይቷል።
ሆኖም ወደ ኤዥያዋ ሀገር ኦማን አምርቶ በተጠናቀቀው ዓመት በሀገሪቱ ሊግ በ31 ነጥቦች ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ ያጠናቀቀውን አል-ሱዋይክ ክለብ በአንድ ዓመት ውል መቀላቀሉን ሶከር ኢትዮጵያ ዘግቧል፡፡

አል-ሱዋይክ የኦማን ሊግን አራት ጊዜ እንዲሁም በቀድሞው የሀገሪቱ መሪ የተሰየመውን የሱልጣን ዋንጫን ሁለት ጊዜ፣ የሀገሪቱን የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ አንድ ጊዜ ማንሳቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.