በጄኔቭ የፀጥታ ማዕከል እና በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ትብብር ሲተገበር የቆየው ፕሮጀክት ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጄኔቭ የፀጥታ ዘርፍ አስተዳደር ማዕከል (DCAF) እና በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ትብብር በልዩ ልዩ ዘርፎች ለሁለት ዓመታት ሲተገበር የነበረው ፕሮጀክት መጠናቀቁ ተገለፀ፡፡
የፀጥታ ዘርፍ ሪፎርምን አስመልክቶ ለፌዴራል ፖሊስ ከፍተኛ አመራሮች በተሰጠው ስልጠና ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል÷ የጄኔቭ የፀጥታ ዘርፍ አስተዳደር ማዕከል በፈረንጆቹ ከ2019 ጀምሮ ለፌደራል ፖሊስ በፀጥታ ዘርፍ በሪፎርም ስራዎች እና በሰው ኃይል አቅም ግንባታ ላይ አስተዋፅኦ ሲያበረክት መቆቱን ገልፀዋል።
የተጀመረውን የሪፎርም ስራ ለማስቀጠል የፀጥታው ዘርፍ የሪፎርሙን እሳቤ እና ጽንሰ-ሀሳብ በመገንዘብ ቀጣይነት ያለው ስራ ለመስራት ስልጠናው ጠቃሚ መሆኑንም ተናግረዋል።
የጄኔቭ የፀጥታ ዘርፍ አስተዳደር ማዕከል ተጠባባቂ ዳይሬክተር እና የኦፕሬሽን ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር ማርክ ዳውንስ በበኩላቸው÷ ዲካፍ በፈረንጆቹ ከ2019 ጀምሮ በሰላም ሚንስቴር እና በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጥያቄ መሰረት ከአውሮፓ ህብረት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ መዋቅር፣ ተቋማዊ የመፈፀም አቅም እና አስተዳደር ከተቋሙ ከፍተኛ አመራር ጋር በመሆን ጥልቅ ጥናት ተካሂዶ በፈረንጆቹ 2020 ለተጀመረው የመጀመሪያው የጋራ ፕሮጀክት እንደመነሻ ሆኖ ማገልገሉን ገልፀዋል።
የጄኔቭ የፀጥታ ዘርፍ አስተዳደር ማዕከል በቀጣይም ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ጋር በትብብር እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡
በዚሁ ወቅት ስለጄኔቭ የፀጥታ ዘርፍ አስተዳደር ማዕከል መርሆዎች ፣ የዓለም አቀፍ የፖሊስ ማሻሻያ ሂደቶች፣ የዓለም አቀፍ የፖሊስ መልካም ተሞክሮዎች እና የፌደራል ፖሊስ ሞዴሎች እንዲሁም የፖሊስ ሪፎርሙ የለውጥ ስራ አመራር ጽንሰ ሀሳብ ላይ የሚያተኩሩ ሰነዶች ቀርበው ውይይት እንደተደረገባቸው ከፌደራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡