Fana: At a Speed of Life!

አፈ-ጉባዔ ፔሎሲ አወዛጋቢ የሆነውን የታይዋን ጉብኝት ጀመሩ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ናንሲ ፔሎሲ አወዛጋቢ ሆኖ የቆየውን የታይዋን ጉብኝታቸውን ጀምረዋል ።

የፔሎሲን የታይዋን ጉብኝት አስመልክቶ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፥ ጉብኝቱን በጥብቅ ማውገዙን ሲጂቲ ኤን ዘግቧል።

ሚኒስቴሩ በመግለጫው ፥ የአፈ-ጉባዔ ፔሎሲ ጉብኝት የ “አንድ ቻይና” መርህን የጣሰ ክህደት ነው፤ አሜሪካውያን በእሳት እየተጫወቱ ነው፥ አሜሪካ የዓለም ሰላም ዋነኛ ጠላት መሆኗንም አረጋግጣለች ማለቱን የዘገበው ደግሞ ኤም ቲቪ ነው።

የቻይና የመከላከያ ሚኒስቴር ለአፈ-ጉባዔ ፔሎሲ የታይዋን ጉብኝት በሰጠው ምላሽ፥ በታይዋን አቅራቢያ ተከታታይ ወታደራዊ ዘመቻ ከዛሬ ጀምሮ እንደሚያካሂድ አስታውቋል።

የአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስቴር የቻይና ባለስልጣናት “እጅግ የከፋ አደገኛ” ያሉትን የአፈ-ጉባዔ ፔሎሲ የታይዋን ጉብኝት ተግባራዊ መሆን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ ይፋ እንዳደረገው፥ የቻይና ሕዝብ ነፃነት ሠራዊት በከፍተኛ ተጠንቀቅ ላይ የሚገኝ ሲሆን፥ ከዛሬ ጀምሮ በታይዋን ሰርጥ ተከታታይ የሆኑና የተመረጡ ወታደራዊ እርምጃዎች ይወሰዳል ብሏል።

የሠራዊቱ ቃል አቀባይ የሆኑት ዉ ኩያን ለቻይና መገናኛ ብዙሃን በሰጡት ማብራሪያ፥ ወታደራዊ እርምጃው የአገሪቱን ብሄራዊ ክብር፣ ሉዓላዊነትና አንድነት ለማስከበር፣ የውጭ ጣልቃገብነትን ለመመከት፥ የታይዋንን ነፃነት ከገንጣዮች ለመከላከል በቆራጥነት የሚወሰድ እርምጃ እንደሆነም ነው ያስታወቁት።

የሠራዊቱ የምሥራቅ ዕዝ የምድር፣ የባህር ሃይልና የአየር ምድቦች በወደቧ ሰሜናዊ፣ ደቡብ ምዕራብና ደቡብ ምሥራቅ አካባቢዎች የተቀናጀ ወታደራዊ ዘመቻ እንደሚያካሂዱም ነው ቃል አቀባዩ ያብራሩት።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.