በአማራ ክልል ዘለቄታዊ እድገት ላይ ያተኮረው ጉባኤ ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአማራ ክልል ዘለቄታዊ እድገት ላይ በማተኮር በባህርዳር ከተማ ሲካሄድ የቆየው የምሁራን ጉባኤ ተጠናቀቀ።
ጉባኤው “የጋራ ራዕይና ግብ ለአማራ ህዝብ ዘለቄታዊ አንድነትና ሁለንተናዊ ስኬት” በሚል መሪ ቃል ነው የተካሄደው።
በሃገሪቱና በክልሉ ወቅታዊ ነባራዊ ሁኔታዎች እንዲሁም ባጋጠሙ ችግሮችና መልካም አጋጣሚዎች ላይ በመምከር ቀጣይ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ተጠናቋል።
በጉባኤው ማጠቃላይ ላይ የወጣው መግለጫ የአማራ ሕዝብና በክልሉ ውስጥ የሚኖሩ ብሔረሰቦች የጋራ ራዕይ እና ግብ ለሁሉም የምትመች ነጻነት፣ ፍትሕ፣ እኩልነት፤ በሕግ የበላይነት ላይ የተመሠረተ ዴሞክራሲ የሰፈነባት እና ጠንካራ ኅብረ-ብሔራዊ አንድነት ያላት፣ ሁሉም ዜጋ በየትኛውም አካባቢ ያለምንም ስጋት ተንቀሳቅሶ የሚኖርባት እንዲሁም ለዜጎቿ እየተሻሻለ የሚሄድ የኑሮ ሁኔታ ማረጋጋጥ የምትችል ኢትዮጵያን እውን ሆና ማየት ነው ብሏል።
በጉባኤው የተሳተፉ ለአማራ ሕዝብ የሚታገሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የፖለቲካ ልሂቃን፣ ምሁራን፣ የማኅበራዊ ሚዲያ አንቂዎች፣ ወጣቶች፣ ብዙኃን ማኅበራት፣ ባለሀብቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት የአማራ ሕዝብና በክልሉ የሚኖሩ ብሔረሰቦች በሀገር አቀፍም ሆነ በክልል ደረጃ የተቀመጡ ራዕዮችና ግቦችን እውን ለማድረግ በጋራ ለመሥራት ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተጠቁሟል።
በተለይም በክልሉ ሕግና ሥርዓት እንዲከበር፣ የንግድና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እንዲነቃቃ እንዲሁም ሥራ አጥነት እንዲቀንስ የሚጠበቅብንን ሁሉ ለማድረግ ቃል ገብተናል ነው ያሉት የጉባኤው ተሳታፊዎች።
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision