ጤና

በደቡብ ክልል 2ኛው ዙር የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ተጀመረ

By Tibebu Kebede

March 13, 2020

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 4 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ክልል 2ኛው ዙር የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ መጀመሩን የደቡብ ክልል ህብረተሰብ ጤና አንስቲትዩት ገለፀ።

የአንስቲትዩቱ ዳይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን እንዳሉት ክትባቱ ከዛሬ ጀምሮ እስከ መጋቢት 7 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ ነው።

ክትባቱ በሲዳማ፣ ሀላባ፣ ከንባታ ጠንባሮ፣ ሀዲያና ወላይታ ዞንን ጨምሮ በስምንት ዞኖች በሚገኙ 54 ወረዳዎች የሚሰጥ ይሆናል።

በዚህም ከ900 ሺህ በላይ ህፃናት ይከተባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

በኢንስቲትዩት የጤና እና ጤና ነክ ድንገተኛ አደጋዎች ቅኝትና ምላሽ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ እንዳሻው ሽብሩ በበኩላቸው፥ በመጀመሪያው ዙር የክትባት ዘመቻ አመርቂ አፈጻጸም መታየቱን ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ዙር በመጀመሪያው የክትባት ዘመቻ የታዩ የቅስቀሳ ጉድለት፣ ትራንስፖርትና የመድሀኒት ብልቃጥ እጥረትን በማስወገድ እንደሚሰራም ገልጸዋል።

በዞኖቹ የሚገኙ ነዋሪዎችም ህፃናት ልጆቻቸውን በማስከተብ ግዴታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

በታምራት ቢሻው

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ! https://t.me/fanatelevision