በጋምቤላ ክልል በዘንድሮው ዓመት 9 ነጥብ 5 ሚሊየን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ እየተሰራ ነው – አቶ ኡሞድ ኡጁሉ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል በዘንድሮው ዓመት 9 ነጥብ 5 ሚሊየን ችግኝ ለመትከል ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ እንደሆነ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ አስታወቁ፡፡
የአኙዋክ ብሔረሰብ ዞን የምክር ቤት አባላትና አመራሮች በጎግ ወረዳ አተቲ ቀበሌ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ-ግብር አካሂደዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው እንዳሉት እንደ ክልል በዘንድሮው ዓመት 9 ነጥብ 5 ሚሊየን ችግኝ ለመትከል ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ ይገኛል።
የተተከሉ ችግኞችን በመጠበቅና በመንከባከብ አድገው ለአካባቢ ጥበቃ እና ለኢኮኖሚ አበርክቶ እንዲውሉ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።
የአኙዋክ ብሔረሰብ ዞን ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ አፒየው ኡዊቲ በበኩላቸው÷ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብሩን ከግብ ለማድረስ የምክር ቤት አባላት በንቃት እየተሳተፉ መሆኑን ገልፀዋል።
የሚተከሉ ችግኞች የምግብ ዋስትናን ለማረጋጥ፣ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እና ለአካባቢ ጥበቃ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ይኖራቸዋል ተብሏል።
ችግኞች በጥሩ ሁኔታ እንዲያድጉ በየጊዜው ምልከታና እንክብካቤ እንደሚያደርጉ የምክር ቤቱ አባላት ቃል መግባታቸውን ከጋምቤላ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!