Fana: At a Speed of Life!

የዓለም ባንክ ለአነስተኛ እና መካካለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች ተጨማሪ 200 ሚሊየን ዶላር መደበ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 129፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም ባንክ ለአነስተኛ እና መካካለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች ተጨማሪ 200 ሚሊየን ዶላር መመደቡን የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት አስታወቀ።

በኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት የአነስተኛ እና መካካለኛ ኢንተርፕራይዝ ፋይናንስ ፕሮጀክት የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ እየተካሔደ ነው።

በምክክር መድረኩ በኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ዋና ዳይሬክተር አቶ ብሩ ወልዴን ጨምሮ የሁሉም ክልሎች አምራች ኢንተርፕራይዝ ሃላፊዎች እና ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

አቶ ብሩ ወልዴ አነስተኛ እና መካካለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች በኢትትዮጵያ ኢንዱስትሪ መር ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው አንስተዋል።

አምራች ኢንተርፕራይዞቹ የታለመላቸውን ግብ እንዲመቱም ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል ነው ያሉት።

የአነስተኛ እና መካካለኛ ኢንተርፕራይዝ ፋይናንስ ፕሮጀክት አስተባባሪ ወይዘሮ የመንዝወርቅ ግረፌ በበኩላቸው፥ ፕሮጀክቱ በሁሉም ክልሎች ካሉት መዋቅሮች ጋር ለዘርፉ እድገት ውጤታማነት የበኩሉን ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ለዚህም የዓለም ባንክ ከዚህ በፊት ከመደበው 276 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ተጨማሪ 200 ሚሊየን ዶላር መመደቡን አስታውቀዋል።

ተጨማሪ በጀቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ላይ የፈጠረውን ጫና ግምት ውስጥ በማስገባት የተፈቀደ መሆኑን ጠቁመዋል።

ፋይናንሱ ለአምራች ኢንተርፕራይዞች ለማሽን ሊዝ አቅርቦት፣ ለስራ ማስኬጃ ብድር እና ለንግድ ስራ ልማት አገልግሎት እንደሚውል ተመላክቷል።

ፕሮጀክቱ ከተጀመረ አንስቶ 4 ሺህ 609 አነስተኛ እና መካካለኛ ኢንተርፕራይዞችን ተጠቃሚ ማድረጉ ነው የተገለጸው።

 

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.