የሲቪል ማኀበረሰብ ድርጅቶች በመንግሥትና በግል ባለሃብቱ የማይሸፈኑ የልማት ሥራዎችን በመተካት ወሳኝ ሚና እየተወጡ ነው – ዶ/ር ዓለሙ ስሜ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሲቪል ማኀበረሰብ ድርጅቶች ከለውጡ በኃላ በመንግሥትና በግል ባለሃብቱ የማይሸፈኑ የልማት ሥራዎችን በመተካት ወሳኝ ሚና እየተወጡ እንደሚገኙ የብልፅግና ፓርቲ ዋና ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሲቪክ ማኅበራት ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር ዓለሙ ስሜ ተናገሩ፡፡
የኢፌዲሪ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን እና ተጠሪ ተቋማቱ ‘ዐሻራችን ለትውልዳችን’ በሚል መሪ ቃል አራተኛውን ዙር የአረንጓዴ ዐሻራ የማስቀመጥ መርሐ ግብር በቡታጂራ አካሂደዋል፡፡
ዶክተር ዓለሙ ስሜ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት÷ ከሀገራዊ ለውጡ በፊት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እንደጸረ ሰላምና ሰላይ የሚታዩበት ሁኔታ አሁን ተቀይሮ ከመንግሥትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብርና በጋራ ሀገር የማልማት ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ነው ብለዋል፡፡
ሀገር የምትበለፅገው አቅምና የተፈጥሮ ሃብትን አስተባብሮ ጥቅም ላይ ማዋል ሲቻል መሆኑን ተቁመው÷ መርሐ ግብሩ አየር ንብረትን ለመጠበቅ ዛፍ ከመትከል ባሻገር አብሮነትንና ወንድማማችነትን በማጠናከር ኢትዮጵያውያን እርስ በእርስ እንድንተዋወቅ እድል የፈጠረ ነው ማለታቸውን የብልፅግና ፓርቲ ጽሕት ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡
የሲቪል ማኀበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ÷ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ለሀገር ልማት በንቃትና ትርጉም ባለው መልኩ እየተሳተፉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ለምለም ምድር ለአዲሱ ትውልድ ማስረከብ የሥራቸው አንዱ አካል መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!