የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ ዲጂታል ኢኮኖሚዋን ለማነቃቃት በዱባይ ቻምበርስ የልምድ ልውውጥ አድርጋለች

By Alemayehu Geremew

August 05, 2022

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ከመንግስት እና ከግሉ ዘርፍ የተወከሉ ልዑካን ቡድኗን ለልምድ ልውውጥ ወደ ዱባይ ኢሚሬትስ መላኳ ተገለጸ፡፡

ከኢትዮጵያ መንግስት ተልዕኮ ወስደው ወደ ዱባይ ያቀኑትን 10 ልዑካንን የመሩት የ”ፔራጎ ኢንፎርሜሽን ሲስተምስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ኩባንያ” ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ እውነቱ አበራ መሆናቸውም ነው የተመላከተው፡፡

ልዑካን ቡድኑ ÷ ዱባይ በዲጂታል ኢኮኖሚ እና አገልግሎቶች የደረሰችባቸውን ስኬቶች መመልከቱም ነው የተገለጸው፡፡

ከልምድ ልውውጡ ባሻገር ኢትዮጵያ የንግድ ሽርክናዎች መመስረት በሚያስችላት ሁኔታዎች ላይ ተወያይተዋልም ተብሏል፡፡

ልዑካን ቡድኑ የኢትዮጵያን የ2025 ዲጂታል ስትራቴጂን የሚደግፉ ስምምነቶችን ለመፈራረም የሚያስችሉ ውይይቶችን ማድረጉም ተገልጿል፡፡

የልዑካን ቡድኑ በኢትዮጵያ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ተወካዮችን እና የ”ፔራጎ ኢንፎርሜሽን ሲስተምስ ተወካዮችን ያካተተ መሆኑን ኢሚሬትስ የዜና አገልግሎት ዘግቧል፡፡

ልዑካን ቡድኑ በአጠቃላይ ሥምንት ስብሰባዎችን ያካሄደ ሲሆን የተወያየውም ከ”ዱባይ ቻምበርስ”፣ ከ”ዲጂታል ዱባይ” ፣”ኦንታይም”፣ “ቫልዩ ግሪድ”፣ “ዲጂታል ፋልኮን” እና “ወርልድ1” ሚዲያን ጨምሮ ከበርካታ ኩባንያዎች ተወካዮች ጋር ነው ተብሏል።

የውይይታቸው ትኩረትም ከኩባንያዎቹ እና ከንግድ ተቋማቱ ጋር በቀጣይ በሽርክና እና በትብብር መስራት በሚችሉባቸው አማራጮች ላይ መሆኑ ነው የተነገረው።