Fana: At a Speed of Life!

የተጠና እርምጃ በመውሰድ በአሸባሪው ሸኔ ላይ ኪሳራ ማድረስ ተችሏል – የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የተጠና እርምጃ በመውሰድ በአሸባሪው ሸኔ ላይ ኪሳራ ማድረስ መቻሉን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም፥ የአሸባሪው ሸኔን ጥቃትን የመከላከልና ቡድኑን የማስወገድ ዘመቻዎች ሲካሄዱ መቆየታቸውን አንስተዋል፡፡

በተለይ በኦሮሚያ ክልልና አዋሳኝ አካባቢዎች የሽብር ቡድኑ እየረበሸ እንደሚገኝ አንስተው፥ በፌዴራልና ኦሮሚያ ክልል የጸጥታ ሃይሉ ጥምረት ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ዘመቻው ሲካሄድ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡

በዘመቻውም ትልልቅ ስኬቶች ተመዝግበዋልም ነው ያሉት፡፡

ሲወሰዱ የነበሩ ዘመቻዎች በተጠኑ ቦታዎች ላይና የተወሰኑ ቦታዎች ዒላማ በማድረግ የሽብር ቡድኑን እንቅስቃሴ ከግምት ውስጥ በማስገባት ሲካሄድ መቆየታቸውን አመልክተዋል፡፡

እንደአብነት ከጥቂት ቀናት በፊት የተወሰደውን እርምጃ አስመልክቶ እንዳሉት ፥ በሆሮጉድሩ ወለጋ ዞን የሱሉላ ፊንጫ ወረዳ ላይ በተፈጸመው እርምጃ በርካታ የሸኔ ታጣቂዎች ላይ እርምጃ ተወስዷል ነው ያሉት፡፡

በአካባቢው የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ ይዞታ የሸንኮራ አገዳ ማሳ ውስጥ በመሸሸግ የተከፈተባቸውን እርምጃ ለመሸሽ ሲሞክሩ እንደነበር አንስተዋል፡፡

በዚህም የተጠና እርምጃ በመውሰድ በአሸባሪው ሸኔ ላይ ኪሳራ ማድረስ ተችሏል ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፡፡

በተወሰደው እርምጃ በርካታ የጦር መሳሪያዎችና የመገናኛ ሬዲዮዎች በቀጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል፡፡

የሽብር ቡድኑ የተለያዩ ግብዓቶችን ሲያከማችበት የነበረውን 69 መጋዝኖችን ከጥቅም ውጭ እንዲሆኑ ተደርጓልም ነው ያሉት።

ከሐምሌ 16 እስከ ሐምሌ 22 በተወሰደው የተቀናጀ ዘመቻ ከ333 በሚሆኑ የሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ ፥ አሸባሪውን ቡድን እያገዙ ነው በሚል የተጠረጠሩ 671 ግለሰቦች በህግ ቁጥጥር ስር ሆነው ጉዳያቸው እየተጣራ ይገኛልም ነው ያሉት፡፡

አሸባሪው ሸኔ ንጹሃን ዜጎች ላይ የሚያሳርፈውን የበቀል እርምጃ በርካታ የመከላከል እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው ብለዋል፡፡

በዚህም የህብረተሰቡ ቀጥተኛ ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ አንስተው ፥ ከጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር የቡድኑን ተልዕኮ በማክሸፉ ላይ እንዲሳተፍና እንዲያግዝ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በመሰረት አወቀ

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.