Fana: At a Speed of Life!

የሐረሪ ክልል በተለያየ ምክንያት ከህዝብ የሚጠብቅባቸውን አገልግሎት መስጠት ባልቻሉ አካላት ላይ ተገቢውን እርምጃ እንደሚወስድ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሐረሪ ክልል በተለያየ ምክንያት ከህዝብ የሚጠብቅባቸውን አገልግሎት መስጠት ባልቻሉ አካላት ላይ ተገቢውን እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል፡፡

ክልሉ በመንግስትና በህዝብ መካከል ያለው መሰረታዊ ግንኙነት የአገልጋይና የተገልጋይ ግንኙነት መሆኑን ገልጿል።

በመሆኑም በየደረጃው ያለው የመንግስት መዋቅር ለህዝቡ ፍትኃዊ ቀልጣፋና ጥራት ያለው መንግስታዊ አገልግሎት ለሁሉም ዜጋ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል ብሏል።

ዜጎችም ያለምንም አድሎና እንግልት መንግስታዊ አገልግሎት የማግኘት መብት አለው ያለው የክልሉ መንግስት በዚህ መነሻነት በየደረጃው ያለው የመንግስት መዋቅር የስራ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን በየጊዜው ማረጋገጥና የማስተካከያ እርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልጋል ነው ያለው።

ወንበር ላይ እያሉ ያላስታወሱትን ህዝብ ከስልጣን ሲነሱ “በእናንተ ምክንያት ነው” ማለት ህዝብን መናቅ ነው!

ከሀረሪ ክልላዊ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተሰጠ የአቋም መግለጫ

በመንግስትና በህዝብ መካከል ያለው መሰረታዊ ግንኙነት የአገልጋይና የተገልጋይ ግንኙነት ነው። በመሆኑም በየደረጃው ያለው የመንግስት መዋቅር ለህዝቡ ፍትኃዊ ቀልጣፋና ጥራት ያለው መንግስታዊ አገልግሎት ለሁሉም ዜጋ ማቅረብ ይጠበቅበታል።

ዜጎችም ያለምንም አድሎና እንግልት መንግስታዊ አገልግሎት የማግኘት መብት አላቸው።

በዚህ መነሻነት በየደረጃው ያለው የመንግስት መዋቅር የስራ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን በየጊዜው ማረጋገጥና የማስተካከያ እርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልጋል።

በመሆኑም በሀረሪ ክልል መንግስት በዋናነት የስራ ውጤታማነትን፣ ብቃትና ስነ ምግባር መነሻ ያደረገ የአመራር ምዘና ለማካሄድ በቂ ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል።

የምዘናው ሂደቱንም ግልጽ በሆኑ መስፈርቶች እና ፍትኃዊ በሆነ መልኩ ለማካሄድ የሚያስችል የአሰራር ስርአት ተዘርግቶ በጥብቅ ዲሲፒሊን ይመራል።

በመጨረሻም ሁሉም አካላት ለህዝብ ካበረከቱት አስተዋፅኦ እና ካገኙት ተጨባጭ ውጤት አንጻር የማስተካከያ እርምጃዎች ይወሰዳል።

በዚህም በስራ ድክመት፣ በብቃት ማነስ ወይም በስነ ምግባር ብልሽት ህዝብ የሚጠብቅባቸውን አገልግሎት መስጠት ባልቻሉ አካላት ላይ ተገቢው እርምጃ የሚወሰድ ይሆናል።

ሆኖም ግን አንዳንድ አመራሮች በስልጣን ዘመናቸው ያላስታወሱትን ህዝብ ግምገማና ምዘና ሲጀመር ውጤታማ ስራ ባለመስራታቸው ቁጭት ሊሰማቸው ሲገባ ህዝቡን “በእናንተ ምክንያት ነው ከወንበሬ የተነሳሁት”ይላሉ።

በስርቆትና ምዝበራ የህዝብ ሀብትን ለግል ጥቅማቸው ሲያግበሱ የነበሩትም ድርጊታቸው ወደ ህግ ሲያመራና ተጠያቂ ሲሆኑ “ማንነቴን”፣ “ብሔሬን” ወይም “ሀይማኖቴን” መነሻ ያደረገ ጥቃት ነው የሚሉም አሉ።

ለመደበኛ ስራቸው ምንም ጊዜ ሳይሰጡ ፣ ተቋማቸውን በአግባቡ ሳይመሩ፣ ጊዜው ባመጣው ማህበራዊ ሚዲያ ብቻ ለገጽታ ግንባታ እያዋለሉ የሚገኙ አመራሮችም የስልጣን ጥማታቸውን በFacebook ጋጋታ ለማርካት ይሞክራሉ።

ደግነቱ ህዝብ እና የጥቅም ተጋሪ ይለያያል። ህዝቡ ማን ምን እንደሆነ ጠንቅቆ ያውቃል።
በስልጣን ዘመንህ ህዝብ የሚፈልገውን ግልጋሎት ሳትሰጥ ቆይተህ ከስልጣን ስትነሳ አድኑኝ ብትል አይሰማህም።

ከህዝብ ሰርቀህና መዝብረህ ለህግ ስትቀርብ “የእናንተ ተወላጅ ስለሆንኩኝ ነው” ብትልም ጆሮ አይሰጥህም።

ባይሆን የቀድሞ ጥፋትን በተለያዩ ሽፋኖች ከማለባበስ ይልቅ ችግሮችን ወደ ውስጥ በማየት የራስ ስህተትን ማረም ተገቢ ነው፣ ሁለተኛ እድልም ያስገኛል።

ስለዚህ ዛሬ ላይ ሆነህ ነገ የማትቆጭበትን አድርግ።
ህዝብን በፍትኃዊነትና በሀቀኝነት አገልግል።

የሀረሪ ክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን
ነሐሴ 1/2014 ዓ.ም
ሀረር

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.