Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባ ከታሪፍ ጋር በተያያዘ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ያለመ ምክክር ተደረገ

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 1 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ ተሽከርካሪዎች መንግስት ባወጣው ታሪፍ ብቻ ህብረተሰቡን በሚያገለግሉበት አግባብ ዙሪያ ምክክር ተደርጓል፡፡

ምክክሩ የተደረገው በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ሰብሳቢነት፣ ከአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ፣ ከትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ፣ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ አዲስ አበባ አሽከርካሪና ተሽከርካሪ ቁጥጥር ባለስልጣን እንዲሁም ከአዲስ አበባ ከንቲባ ፅህፈት ቤት የስራ ሃላፊዎች ጋር በጋራ በመሆን ነው፡፡

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ መንግስት የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተሸከርካሪዎችን ብቻ በመለየት ድጎማ ማድረግ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

ትግበራው ውጤታማ የሚሆነው ተደጓሚ ተሽከርካሪዎቹ በተቀመጠው ታሪፍ መሠረት ብቻ ማገልገል ሲችሉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ይሁንና በአዲስ አበባ ከተማና በተቀሩትም የሀገራችን ክፍሎች በታሪፍ የማገልገልና የመገልገል ሁኔታ ውስን መሆኑን በመግለፅ ቁጥጥር ሊደረግ ይገባል ነው ያሉት።

ከክልልና ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት መዋቅር ጋር በጋራ በመሆን ህብረተሰቡ በተቀመጠው ታሪፍ ብቻ እንዲገለገል ለማድረግ የሚያስችል ምክክር መደረጉን እና ክልሎች እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ግብረሃይል በማደራጀት ጭምር ቁጥጥር ማድረግ መጀመራቸውን አንስተዋል፡፡

በሌላ በኩል በመላ ሀገሪቱ የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ የሆኑ ከ141 ሺህ በላይ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎችን በማገልገል ላይ የሚገኙ የነዳጅ ማደያዎች ያላቸውን ሚና በአግባቡ እንዲወጡ ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ ቁጥጥርን ማጠናከር እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡

የድጎማ ስርአቱ የታለመለትን ግብ እንዲመታ የታሪፍ ቁጥጥር ማድረግ ወሳኝ በመሆኑ ከትራንስፖርት ተቆጣጣሪዎችና ከፀጥታ መዋቅሮች ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚገባ መግለጻቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.