Fana: At a Speed of Life!

የአሸባሪው ሸኔ የደቡብ ዞን ምክትል ሀላፊ በቁጥጥር ስር ዋለ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሸባሪው ሸኔ የደቡብ ዞን ምክትል ሀላፊ የሚል ሀላፊነት የተሰጠው ተጠርጣሪ በቤት መኪና ወደ መሀል ሀገር ሲጓዝ በቦረና ዞን ሞያሌ ወረዳ በቁጥጥር ስር መዋሉን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ ገለጸ፡፡
የመምሪያው ኮሙኒኬሽን ረዳት ዲቪዥን ሀላፊ ኢንስፔክተር ግርማ ሹሚ ተጠርጣሪው በሞያሌ ወረዳ ልዩ ስሙ ቦቆላ በተባለ ስፍራ በቁጥጥር ስር መዋሉን ተናግረዋል።
ተጠርጣሪው ከአዳማ ከተማ በተላከለት መኪና በመጓዝ ላይ እንዳለ በፖሊስ በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ ሐምሌ 30 ቀን 2014 ዓ.ም ከቀኑ 8 ሰአት አካባቢ በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገልጿል፡፡
በቁጥጥር ስር የዋለው ተጠርጣሪ ቀድሞ የሚታወቅበትን ‘መሀመድ አሜ’ የሚለውን የመጠሪያ ስሙን አብዱ ኡመር ሁሴን በሚል ቀይሮ መታወቂያ በማሰራት ሲንቀሳቀስ እንደነበር ነው የተገለጸው፡፡
ግለሰቡ ከአሸባሪው የሸኔ ቡድን ጋር ብቻ ሳይሆን አልሻባብን ከመሳሰሉ ዓለም አቀፍ አሸባሪዎች ጋር ግንኙነት እንዳለው የሚጠረጠር እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
የቦረና ዞን ፖሊስ ተጠርጣሪውን ጭኖ የነበረውን መኪና ከእነአሽከርካሪው በቁጥጥር ስር አውሎ ጉዳዩን በመከታተል ላይ እንደሆነ መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.