Fana: At a Speed of Life!

በ2015 በጀት ዓመት የክልሉን ሠላም በማጠናከር ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ስራዎች ይከናወናሉ -አቶ አሻድሊ ሀሰን

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በ2015 በጀት ዓመት የክልሉን ሠላም የበለጠ በማጠናከር ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ስራዎች እንደሚከናወኑ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ገለጹ።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን÷ በክልሉ የ2015 በጀት ዓመት መሪ-ዕቅድ ላይ ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮችና የተቋማት ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል።
የክልሉ መሪ ዕቅድ የ2014 ዓ.ም የማጠቃለያ ምዕራፍ ግምገማን መነሻ አድርጎ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
ባለፉት ዓመታት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የነበረው የጸጥታ ችግር ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደርጋሉ ተብለው በዕቅድ የተያዙ የልማት ስራዎችን በተፈለገው ልክ ለመፈጸም ከፍተኛ ጫና አሳድሮ ቆይቷል ብለዋል።
በ2015 በጀት ዓመት የክልሉን ሠላም ከማጠናከር ጎን ለጎን ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የተያዙ የልማት ስራዎችን ለማከናወን ከፍተኛ ጥረት ማድረግ እንደሚገባም አቶ አሻድሊ ገልጸዋል።
የግብርና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ከፍተኛ የርብርብ ማዕከል ተደርጎ ይሠራል ያሉት አቶ አሻድሊ÷ ግብርናውን ሜካናይዝድ ለማድረግ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።
የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደቀያቸው ከመመለስና ከመደገፍ በተጨማሪ መልሶ ለማቋቋም በትኩረት እንደሚሠራም ነው የተናገሩት።
የክልሉን ሠላም አሁን ካለበት የበለጠ ለማጠናከር እንደሚሠራ ጠቁመው÷ ከምንም በፊት ሠላምን ማረጋገጥ ከተቻለ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የተያዙ ዕቅዶችን ማሳካት ይቻላል ብለዋል።
የኑሮ ውድነትን ለመከላከል አቅርቦቱን ማሻሻል እና የተቀመጡ የመፍተሔ እርምጃዎችን በአግባቡ መተግበር እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ዕቅዱን ውጤታማ ለማድረግ ህገ-ወጥነትንና ሌብነትን መቆጣጠር ይገባል ያሉት አቶ አሻድሊ÷ ለዕቅዱ አፈጻጸም ሂደት የተለየ ክትትል እንደሚደረግ አስረድተዋል።
የክልሉ ተቋማት ኃላፊዎች÷ በተቀናጀ መልኩ በመስራት እና በአፈጻጸም ሂደት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን መፍትሔ በመስጠት ዕቅዱን ውጤታማ ለማድረግ እንደሚሠሩ መግለጻቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.