የሀገር ውስጥ ዜና

በአሶሳ ዞን በሸርቆሌ ወረዳ ከ23 በላይ የፀረ-ሰላም ቡድን አባላት መደምሰሳቸው ተገለፀ

By Melaku Gedif

August 08, 2022

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሶሳ ዞን ሸርቆሌ ወረዳ በጥምር የፀጥታ ኃይሉ በተካሄደ ዘመቻ በአካባቢው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ከ23 በላይ የፀረ-ሰላም ቡድን አባላት መደምሰሳቸው ተገለፀ፡፡

የሸርቆሌ ወረዳ ሠላም ግንባታና ፀጥታ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብዱልባሲጥ አጣሂር እንደገለጹት፥ የፀረ-ሰላም ቡድኑ ከሐምሌ ወር መግቢያ ጀምሮ በወረዳው ሰርጎ በመግባት በህብረተሰቡ ላይ ጥቃት ለማድረስ አቅዶ ሲንቀሳቀስ ቀይቷል፡፡

ይሁን እንጂ የወረዳው ጥምር የፀጥታ ኃይል በተጠና መልኩ ባካሄደው የኦፕሬሽን ስራ ከ23 በላይ የሚሆኑ የፀረ-ሰላም ቡድኑ አባላትን ጨምሮ ሁለት የመጠለያ ካምፖቹን መደምሰስ መቻሉን ኃላፊው ገልፀዋል፡፡

አክለውም ፀረ-ሰላም ቡድኑ በአሁኑ ሰዓት በጥምር የጸጥታ ኃይሉ የሚደርስበትን ምት መቋቋም ተስኖት የያዘውን የጦር መሳሪያ እና መገናኛ ሬዲዮኖችን ጥሎ መሸሹን እና አንዳንዶቹ አባላቱ ደግሞ እጃቸውን ለፀጥታ ኃይሉ መስጠታቸውን አስረድተዋል፡፡

የወረዳው የፀጥታ ሁኔታ አሁን ላይ መሻሻል ማሳየቱን የገለፁት ኃላፊው፥ ይህ አንፃራዊ ሰላም ተጠናክሮ እንዲቀጥል የወረዳው ማህበረሰብ ከጸጥታ ኃይሉ ጋር እያደረገ ያለውን ሁለተናዊ ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠል አለበት ሲሉ ማሳሳባቸውን ከሸርቆሌ ወረዳ ኮሙኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!