Fana: At a Speed of Life!

ተመድ ለእስራኤል እና ፍልስጤም ግጭት ዘላቂ መፍትሄ እንዲሰጥ ጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የመካከለኛው ምሥራቅ የሰላም ሂደት ልዩ አስተባባሪ ቶር ዌንስላንድ የሁለቱን ወገኖች ግጭት በዘላቂነት የሚያስቆም ውይይት እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።

በፍልስጤም እና በእስራኤል በትናንትናው ዕለት የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት አስተማማኝ አለመሆኑን  ነው ልዩ አስተባባሪው የሚገልጹት።

ያለፉት ቀናት በጋዛ ሰርጥ በእስራኤል ወታደራዊ ኃይሎች እና በፍልስጤም ታጣቂ ቡድኖች በተለይም በፍልስጤም እስላማዊ ጂሃድ መካከል የተፈጠረው ግጭት  አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ዌንስላንድ በመካከለኛው ምሥራቅ  የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ተናግረዋል።

የፍልስጤም ኢስላማዊ ጂሃድ እና የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረሳቸውን በተለያዩ መግለጫዎች ማስታወቃቸውንና  የተኩስ አቁም ስምምነቱም እስካሁን መዝለቁን ጠቁመዋል።

ይሁን እንጂ የተኩስ አቁም ስምምነቱ አስተማማኝ አይደለም ያሉት ዌንስላንድ፥  ዳግም ወደ ጦርነት መግባት በፍልስጤማውያን እና በእስራኤላውያን ላይ አስከፊ መዘዝ ከማስከተል በቀር ፖለቲካዊ ለውጥ አያመጣም ሲሉ  አስታውቀዋል፡፡

ዌንስላንድ የእስራኤል እና የፍልስጤም መሪዎች ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር በመሆን ትርጉም ወዳለው ድርድር እንዲገቡና ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን እንዲያጠናክሩ በድጋሚ ጥሪ አቅርበዋል።

እንደዚህ ያሉ የጥቃት ዑደቶች የሚቆሙት ችግሩ ፖለቲካዊ መፍትሄ ሲያገኝ ብቻ መሆኑን የገለጹት  አስተባባሪው፥  ግጭቶች መቋጫ የሚያገኙት የሁለቱን መንግስታት መፍትሔ መሰረት በማድረግ በ1967 መርሆች፡ በተባበሩት መንግሥታት ውሳኔዎች ፣ በዓለም አቀፍ ሕጎች እና ቀደም ሲል በተደረጉ ስምምነቶች መሠረት መሆን ይኖርበታል ብለዋል።

ምንጭ፡- ሲጂቲኤን

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.