Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያና በደቡብ ለድርቅ ተጋላጭ አካባቢዎች የእንስሳት መኖ እየለማ ነው

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች ለድርቅ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የእንስሳት መኖ ልማት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የግብርና ቢሮ ኃላፊዎች ገለጹ።

የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ አበራ ወርቁ ÷ የእንስሳትን ምርታማነት ለማሳደግ ፣ ዝርያ ለማሻሻልና የእንስሳት በቂ መኖ ለማቅረብ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ቦረናን ጨምሮ በድርቅ በሚጠቁ አካባቢዎች የእንስሳት መኖን በመስኖ ለማልማት የውሃ ግድብ መሰረተ ልማት ላይ በስፋት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ ደረጃቸው ቢለያይም በድርቅ የሚጠቁ ከ10 የማያንሱ አካባቢዎች እንዳሉ ገልፀው፣ በ2015 በጀት ዓመት በድርቅ በሚጠቁ አካባቢዎች ከ90 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት ለመኖ ልማት መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

በክረምት ወቅት ቁጥቋጦ አካባቢዎችን በሳር መተካት እንዲሁም በበልግ ዝናብ እና በመስኖ መኖን በማልማት እንደሚከወን ተናግረዋል።

ከመኖ ባሻገርም ለእንስሳት የውሃ አቅርቦት ከወዲሁ ለመስራት ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

የደቡብ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ዑስማን ሱሩር በበኩላቸው ÷ የተቀናጀ ግብርና በምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ዓይነተኛ መፍትሄ እንደሆነ ገልፀው ፣ በእንስሳት ሐብት ልማት ላይ ማተኮር ያስፈልጋል ብለዋል።

እንደ ሀገር 22 ቢሊየን ሊትር የወተት ምርት በዓመቱ እንደሚጠበቅ ገልጸው፣ የወቅቱ ምርት ግን በዓመት ከ7 ቢሊየን ሊትር እንደማይበልጥ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ክልሉ በእንስሳት ማዳቀል ላይ በስፋት እየሰራ ሲሆን ለዚህም በቤተሰብ ቢያንስ 400 ካሬ ሜትር እንስሳት መኖ አልምቶ ከራሱ አልፎ ለሌሎችም መሸጥ እንዲችል የማድረግ ግብ ሰንቆ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም በተለይም በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎች የመኖ እጥረት እንዳይከሰት በቂ መኖ የማምረት ስራ በትኩረት እንደሚከናወንም ገልጸዋል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.