Fana: At a Speed of Life!

በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር በኢንተርፖል ሲፈለግ የነበረ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር ዋለ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 4 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያን ጨምሮ በሱዳን፣ ሶማሊያ እና ኤርትራን በመሳሰሉ ሀገራት በተደራጀ መረብ በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ውስጥ በመግባት እና የወንጀል ድርጊቱን በመምራት በዓለም አቀፉ የፖሊስ ተቋም (ኢንተርፖል) ሲፈለግ የነበረ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር መዋሉን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

ኪዳኔ ዘካርያስ ሀፍተማርያም የተባለው ተጠርጣሩ ከአምስት ግብረአበሮቹ ጋር በቁጥጥር ስር መዋሉንም ነው ኮሚሽኑ ያስታወቀው።

ስድስቱም ተጠርጣሪዎች በሰው የመነገድ እና ሰውን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር በማሻገር ወንጀል የሚፈፅሙ ሦስት እና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች የያዘ የተደራጀ የወንጀል ቡድን በመመስረት ሲንቀሳቀሱ እንደነበርም ገልጿል።

ወንጀሉ ከአፍሪካ ቀንድ እስከ አውሮፓ ድረስ በተዘረጋ፣ ውስብስብና የተቀናጀ የወንጀል ቡድን ከስደተኞች ከፍተኛ መጠን ያለው የገንዘብ ጥቅም ለማግኘት እንደሚሰራም የፖሊስ ምርመራው ያስረዳል።

በተለይም የየሀገራቱ ዜጎች የእገታ፣ አስገድዶ መድፈር፣ እስራት፣ ድብደባ፣ ግርፋት እና ግድያ ወንጀሎች መጠቃታቸውም ተጠቁሟል።

በዚህም 1ኛ ተጠርጣሪ ኪዳኔ ዘካርያስ ለረጅም አመታት በኢንተርፖል እና በዩሮፖል ሲፈለግ ቆይቶ ከየካቲት 3 እስከ መጋቢት 3 ቀን 2012 ዓ.ም ባሉት የተለያዩ ቀናት ከግብረአበሮቹ ጋር በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው ይገኛል።

የወንጀል ምርመራው በፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ፣ በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ፣ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ በብሄራዊ መረጃና ደህንነት የብሄራዊ መረጃ ማዕከል፣ በኢንተለጀንስ ኔትወርክ ሴኩዩሪቲ ኤጀንሲ፣ በደህንነት መረብ እና በኢትዮ ቴሌኮም ቅንጅት በልዩ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑ ተገልጿል።

በድርጊቱ ተጎጂ የነበሩ ግለሰቦች በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮ ቀርበው በቂ ሰነድ በመያዝ አቤቱታ እንዲያቀርቡ መጠየቁን ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.