Fana: At a Speed of Life!

ትራምፕ ለዓቃቤ ሕግ ቃላቸውን ለመስጠት አሻፈረኝ አሉ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ለሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች ቃላቸውን ለመስጠት አሻፈረኝ ማለታቸው ተገልጿል፡፡
ድርጅታቸው ለአበዳሪዎች፣ ለመድን አገልግሎት ሰጪዎች እና ለግብር አስከፋይ አካላት አሳሳች የፋይናንስ መግለጫዎችን በማቅረብ የሕግ መተላለፍ ጥያቄ የቀረበባቸው ትራምፕ፥ ከሦስት ዓመታት በላይ በቆየው የፍትሐ ብሔር ምርመራ በኒውዮርክ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሌቲሺያ ጀምስ ፅሕፈት ቤት ጠበቆች በኩል ምላሽ እንዲሰጡ መጠየቃቸው ተገልጿል፡፡
ክሳቸውም በፍትሐ ብሔር የሚታይ ጉዳይ እንደሆነ ነው የተመለከተው።
ይሁን እንጂ ትራምፕ በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የቀረበላቸውን ጥያቄ በሚመለከት የአሜሪካ ሕገ መንግሥት አምስተኛ ማሻሻያን በመጥቀስ “መልስ ያለመስጠት መብት” እንዳላቸው ነው የገለጹት፡፡
አምስተኛው የአሜሪካ ሕገ መንግሥት ማሻሻያ “ ማንኛውም ሰው በተጠረጠረበት ጉዳይ ላይ ቃሉን የመስጠት ግዴታ የለበትም” ስለሚል።
በጉዳዩ ላይ መግለጫ የሰጡት ትራምፕ፥ በአሜሪካ ሕገ መንግሥት እና በሕግ አማካሪዬ ምክር መሠረት በልዩ መብቶች ውስጥ የሚካተቱ ጥያቄዎችን ለመመለስ ፈቃደኛ አይደለሁም ሲሉም ተናግረዋል።
ትረምፕ ዛሬ ማለዳ ላይ በማህበራዊ ሚዲያ ገፃቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፥ “ታላላቅ ኩባንያዎቼ እና እኔ ከሁሉም አቅጣጫ በአምባገነኖች ቡድን በየአቅጣጫው እየተጠቃን ነው” ብለዋል።
ጥቁር አሜሪካዊ የሆኑት ዓቃቤ ሕግ ጄምስን “ዘረኛ” እና “አምባገነን” እንደሆኑ አድርገው እንደሚመለከቷቸውም ነው ዶናልድ ትርምፕ የገለጹት።
ቀደም ሲልም ከትረምፕ በተጨማሪ ሁለቱ ትልልቅ ልጆቻቸው በአባታቸው ጉዳይ ላይ ቃላቸውን እንዲሰጡ የኒው ዮርክ ከተማ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ፅሕፈት ቤት ማስታወቁ ይታወሳል።
በሌላ በኩል በጆርጂያ የሚገኝ ፍርድ ቤት በ 2020 የግዛቲቱን ምርጫ ውጤት የማደናቀፍ ሙከራዎችን በሚመለከትየዶናልድ ትራምፕ የቀድሞ ጠበቃ ሩዲ ጁሊያኒ በአትላንታ ልዩ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ትናንት ትእዛዝ መስጠታቸው ተነግሯል።
ነገር ግን ጁሊያኒ ጤንነታቸው ወደ ግዛቱ ለመብረር እንደማይፈቅድላቸው በመግለፅ አሻፈረኝ ቢሉም፤ ምላሻቸው ዳኛውን ማሳመን ያልቻለ እንደሆነም ተመላክቷል፡፡
የአሜሪካ የፌዴራል ምርመራ ቢሮ ( ኤፍ ቢ አይ ) የቤተ መንግስት ከፍተኛ ምስጢራዊ ሰነዶችን ለማሰስ በሚል ፍሎሪዳ ግዛት በሚገኘውና ማራ ላጎ በተሰኘው በታላቁ የዶናልድ ትራምፕ መኖሪያ ቤት ላይ ትናንት ድንገተኛ ፍተሻ ማድረጉ ይታወሳል።
ምንጭ፡- ሲኤንኤን እና ዘ ጋርዲያን
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.