የሀገር ውስጥ ዜና

ለጋራ ዓላማ በአንድነት ከቆምን ፈተናን አሸንፈን በድል እንደምንሻገር የህዳሴ ግድብ ምስክር ነው – ብልፅግና ፓርቲ

By Meseret Awoke

August 11, 2022

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ብልጽግና ፓርቲ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ተርባይን ሃይል በማመንጨቱ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክቱን አስተላለፈ፡፡

ፓርቲው ፥ የኢትዮጵያዊነታችን ዓርማ የጋራ ጥረታችን አሻራ የሆነው ታላቁ የህዳሴ ግድባችን ሁለተኛ ተርባይን ሀይል ላመነጨበት ለዚህ ታሪካዊ ቀን እንኳን አደረሳችሁ እንኳን አደረሰን ብሏል።

ስለኢትዮጵያችን ብልጽግና የጋራ ራዕይ ሰንቀን በጋራ ጀመርን፣ ውጣ ውረዱን ሁሉ በጋራ ተጋፈጥን፤ ያሰብነውን ከማሳካት ማንም እንደማያስቆመን በተግባር አሳየን ሲልም በማህበራዊ ትስስር ገጹ መልዕክቱን አጋርቷል።

እኛ ኢትዮጵያዊያን ለጋራ ዓላማ በአንድነት ከቆምን ማንኛውንም ፈተና አሸንፈን በድል እንደምንሻገር ታላቁ የህዳሴ ግድባችን ህያው ምስክራችን ነው ሲልም ነው ፓርቲው የገለጸው።

ኢትዮጵያውያን ሁሉ ፕሮጀክቱ ለዛሬው ስኬት እንዲበቃ በገንዘብ፣ በእውቀት፣ በጉልበትና በሀሳብ አሻራ ማኖሩን የገለጸው ፓርቲው ፥ እንኳን የልፋታችሁን ዋጋ ለማየት በቃችሁ ብሏል፡፡

ታላቁ የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያዊያን ሁሉ የጋራ ሀብት ብቻ ሳይሆን የሉዓላዊነታችንና የአገራዊ ክብራችን መገለጫ አርማ ነው፤ ልፋታችሁ ፍሬ እያፈራ ይቀጥላልም ነው ያለው።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!