የሀገር ውስጥ ዜና

በኢትዮ-ጂቡቲ የድንበር አገልግሎት ግንባታ ለማስጀመር የሚያስችል ድጋፍ ተገኘ

By Alemayehu Geremew

August 11, 2022

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 5 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ)በኢትዮ-ጅቡቲ ጋላፊ ድንበር የአንድ – አለቅ የድንበር አገልግሎት ግንባታ በ3 ነጥብ 2 ሚሊየን ዩሮ የድጋፍ በጀት እንዲጀመር “ከኮሜሳ” ጋር ስምምነት ላይ ተደረሰ፡፡

በቀጣይ የፕሮጀክቱ አፈጻጸም እየታየ ድጋፉ እንደሚቀጥልም የንግድና ቀጣናዊ ትሥሥር ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ ከምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ኢኮኖሚ ገበያ (ኮሜሳ) ዋና ፀሃፊ ቼልሺ ካኣፕዋፒዊ ጋር በዛምቢያ-ሉሳካ በተወያዩበት ወቅት ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም በኢትዮ-ኬንያ ድንበር በሞያሌ ከተማ ዘመናዊ የገበያ ማዕከል ለመገንባት በሚቀጥለው ዓመት ጥናቱ ተጠናቆ የግንባታ ሥራ እንዲጀመር ውሳኔ ላይ መደረሱንም የንግድና ቀጣናዊ ትሥሥር ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡

ይህም ኢትዮጵያ ለጀመረችው ቀጣናዊ ኢኮኖሚያዊ ትስስር አጋዥ ኃይል እንዲሚሆን ተስፋ ተጥሎበታል ተብሏል፡፡