Fana: At a Speed of Life!

በስራ አጥነት ችግሮችና በስራ ፈጠራ ላይ ትኩረቱን ያደረገ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 5 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ትኩረቱን በስራ አጥነት ችግሮችና በስራ ፈጠራ ላይ ትኩረቱን ያደረገ ሃገር አቀፍ የውይይት መድረክ በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት እየተካሄደ ነው።

በውይይት መድረኩ ላይ በምስራቅ ኢትዮጵያ የሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ኢንዱስትሪዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈውበታል።

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና ተማሪዎች ጉዳይ ምክትል ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጀይላን ወልዩ እንዳሉት በአሁኑ ወቅት ስራ አጥነት የሃገራችን ብሎም የዓለም ችግር መሆኑን ገልፀዋል።

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትም የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስርን በማጠናከር የስራ ሃሳብ ያላቸውን የስራ ፈጣሪዎች ሃሳባቸው ወደ ተግባር እንዲሸጋገር መደገፍ ይገባል ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው ባዘጋጀው የመጀመሪያው ሃገር አቀፍ የስራ አጥነት ችግር እያስከተለ ባለው አደጋና በመፍትሔ ሃሳብነት በሚቀርቡ ጥናትን መሰረት ባደረጉ የምርምር ውጤቶች ላይ በመነጋገር ችግሩን ዘላቂ በሆነ መንገድ መቀነስ እንደሚቻልም ተናግረዋል።

በመድረኩ ላይ በኢትዮጵያ ከሚገኙ ወጣቶች መካከል 27 በመቶዎቹ ለስራ አጥነት ችግር የተጋለጡ መሆናቸው ተነስቷል።

ለዚህም የገጠር መሬት በየጊዜው መጥበብ፣ ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረግ ፍልሰትና የግል ኢንዱስትሪዎችና ተቋማት በሚፈለገው ልክ የስራ እድሎችን መፍጠር አለመቻላቸው ምክንያት መሆኑ ተጠቅሷል።

ለሁለት ቀናት በሚካሄደው የውይይት መድረክ ላይ የተለያዩ ጥናታዊ ፅሑፎች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል።

በተሾመ ኃይሉ

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.