Fana: At a Speed of Life!

የህዳሴ ግድብ ለየትኛውም ጫና ሳይበገር ለስኬት መብቃቱ የትውልዱ ፅናት እና ትብብር ማሳያ ነው- አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 6 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የታላቁ ህዳሴ ግድብ በየትኛውም ሰው ሰራሽ ጫና ሳይበገር ለስኬት መብቃቱ የትውልዱ ፅናት እና ትብብር ማሳያ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ፡፡

አቶ ደመቀ የሕዳሴ ግድብ ሶስተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ማብሰሪ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት÷ለዘመናት ቁጭት እያወረሰ ይፈስ የነበረው የአባይ ወንዝ ደረጃ በደረጃ የተግባር ምላሹን እያጠበቀ ለሁለተኛ ዙር ሃይል በማመንጨት ታላቅ የታሪክ ምዕራፍ ላይ ደርሷል ብለዋል።

የአንድነታችን መገለጫ የህብረታችን ማረጋገጫ የሆነው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት በሂደት ወደ ማጠናቀቂያ ምዕራፍ መሸጋገሩን ቀጥሏል ሲሉም አውስተዋል፡፡

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት በማንኛውም ሰው ሰራሽ ጫናዎች ሳይበገር ለዚህ ታላቅ ውጤት መብቃቱ የትውልዱ ፅናት እና ትብብር ማሳያ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት እንደሃገር ከገጠሙን የሰላምና የፀጥታ ችግሮች አኳያ የግድቡ ግንባታ ሳይስተጓጎል በተቀመጠለት የጊዜ ማዕቀፍ ማስቀጠል መቻላችን ፈተና ይበልጥ ያፀናን እንደሆን እንጂ ከቶውኑ እንደማይጥለን በተግባር ያረጋገጥንበት ነውም ብለዋል።

አቶ ደመቀ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሶስተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በቀሪ የማጠናቀቂያ ምዕራፍ ስራዎች በተለመደው አግባብ ሁሉም ኢትዮጵያዊ አንድነቱን ይበልጥ እንዲጠብቅ እና ህብረቱን እንዲያፀና ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.