Fana: At a Speed of Life!

አሽከርካሪውን የገደሉት ጓደኛማቾች በእድሜ ልክ ፅኑ አስራት ተቀጡ

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 6 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ አንድ የራይድ አሽከርካሪን የገደሉ ጓደኛማቾች በእድሜ ልክ ፅኑ እስራት መቀጣታቸው ተገለፀ፡፡

1ኛ ተከሳሽ የአብስራ ሰለሞን እና 2ኛ ተከሳሽ በላይነው ንጉስ ካልተያዘው ግብረ-አበራቸው ጋር በመሆን ነሕሴ 6 ቀን 2012 ዓ.ም ከምሽቱ 2፡30 ሰዓት ራይድ ጠርተው አሽከርካሪውን በንፋስ ስልክ ክ/ከተማ ወረዳ 12 ክልል የሰዎች እንቅስቃሴ ወደማይበዛበት ገባ ያለ ቦታ ጠርተውት ሆራ ትራዲንግ ተብሎ የሚጠራው ስፍራ ሲደርሱ 2ኛ ተከሳሽ እና ያለተያዘው ሌላ ግብረ-አበራቸው አሽከርካሪ ንጉስ ከፍያለውን አንገቱን አንቀው በመያዝ ወንበር ስር ማስተኛታቸው ተገልጿል፡፡

1ኛ ተከሳሽ መኪናውን እየነዳ ሟችን ወደኋላ በመዞር በተደጋጋሚ በጩቤ ሆዱ ላይ በርካታ ቦታ በመውጋት ህይወቱ ሲያልፍ፥ የሟችን ቪትስ መኪና፣ የሞባይል ስልክ እና ጫማውን አጠቃላይ 758 ሺህ 250 ብር የሚያወጣ ንብረት ዘርፈው ተሰውረዋል፡፡

ይህን ተከትሎ ፖሊስ ባደረገው ክትትል በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ ሲደረግ ቆይቶ፥ በፈፀሙት ከባድ የውንብድና ወንጀል በፍትሕ ሚኒስቴር ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ ክስ መስርቶባቸዋል፡፡

ተከሳሾች ፍ/ቤት ቀርበው የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሲጠየቁ፥ ድርጊቱን አልፈፀምንም በማለት ክደው የተከራከሩ ሲሆን÷ ዐቃቤ ሕግ የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎች በማቅረብ ማስረዳቱን ከፍትህ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ግድያ እና ከባድ ውንብድና ችሎትም የዐቃቤ ሕግ እና የተከሳሾችን ክርክር ሲከታተል ከቆየ በኋላ፥ ተከሳሾች በተከከሰሱበት አንቀፅ ስር ጥፋተኛ ናቸው በማለት እያንዳንዳቸው በእድሜ ልክ ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኖባቸዋል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.