Fana: At a Speed of Life!

አዳማ ጄነራል ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ፣ ደብረ ታቦርና ዋቻሞ ዩኒቨስቲዎች ተማሪዎቻቸውን አስመረቁ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአዳማ ጄነራል ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ፣ ደብረ ታቦርና ዋቻሞ ዩኒቨስቲዎች በተለያየ የሙያ ዘርፍ ያሰለጠኗቸውን ተማሪዎቻቸውን በዛሬው እለት አስመርቀዋል።

የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ በድህረ ምረቃ በመደበኛ እና በተከታታይ መርሀግብር ያስተማራቸውን 1 ሺህ 223 ተማሪዎቹን በዛሬው እለት አስመርቋል።

ዩኒቨርሲቲው ከአምስት ኮሌጆች በ11 የትምህርት መሰኮች ያስተማራቸውን ተማሪዎቹን ያስመረቀ ሲሆን፥ ከነዚህ በህክምና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በቅድመ ምረቃ በህክምና ዶክትሬት እና በድህረ ምረቃ በህብረተሰብ ጤና የትምህርት መስኮች 36 ወንዶች እና 6 ሴቶች በአጠቃላይ 42 ተመራቂወች ይገኙበታል።

በስነስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የሳይንስና እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ድኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ፥ የህክምና ዘርፍ ትልቅ እውቀት እና ብዙ ትዕግስት እንደሚያስፈልገው ገልጸዋል።

የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ሀብታሙ አበበ በበኩላቸው፥ ተመራቂዎች የተማሩትን ትምህርት የሰዎችን ችግር በመፍታት እንዲሁም በጥናት እና ምርምር እንዲያዳብሩ ጠይቀዋል።

የአዳማ ጄነራል ሆስፒታል እና ሜዲካል ኮሌጅን በህክምና ዲግሪ ያሰለጠናቸውን ተማሪዎችን በዛሬው እለት አስመርቋል።

ሜዲካል ኮሌጁ ዛሬ 15 ተማሪዎች በዶክትሬት ያስመረቀ ሲሆን 1 ሺ 300 የሚሆኑ ተማሪዎች በምህርት ላይ እንደሚገኙ የኮሌጁ ዲን ድሪባ ደገፋ ገልፀዋል።

በመድረኩ የተገኙት የጤና ሚንስትር ድኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ፥ ተመራቂ የጤና ባለሞያዎች በዘርፉ ያለውን የህክምና ጥራት ችግር ለመቅረፍ እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ ለመጀመሪያ ጊዜ በሀይብሪድ ኢኖቬቲቭ ካሪኩለም በዶክትሬት ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 26 ተማሪዎችን እና 33 የሕክምና ዶክተሮችን በዛሬው እለት አስመርቋል።

በምረቃው ላይ የተገኙት የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አፈወርቅ ካሱ፥ ተመራቂዎቹ ቃለ መሀላ በገቡለት የሕክምና ሥነ-ምግባር በመታገዝ ቅን አገልጋዮች እንዲሆኑ አሳስበዋል።

ከዚህም ባለፈ በተግባር በተደገፈው ሀይብሪድ ኢኖቬቲቭ ካሪኩለም የቀሰሙትን የሕክምና ትምህርት የሀገሪቱን ብሎም የዓለምን ህዝብ ስጋት ላይ ከጣሉ ዘመን ወለድ የጤና ችግሮች ኅብረተሰቡን ለመታደግ ተግባራዊ እንዲያደርጉት ጥሪ አቅርበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.