ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የእንጦጦ ፕሮጀክትን ጎበኙ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በአዲስ አበባ እንጦጠ እየተካሄደ ያለውን የእንጦጦ ፕሮጀክት ጎብኝተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጉብኝቱን አስመልክቶ በፌስቡክ ገፃቸው ላይ፥ ከተሞቻችን አንጡራ ሀብት በውስጣቸው ይዘዋል ብለዋል።
“በእንጦጦ ፕሮጀክት ጉብኝት እንደተመለከትሁት፣ ለውጡ አስደናቂ ነው። ሥራው ሲጠናቀቅ ደግሞ አያሌ የቱሪስትና የሥራ ዕድሎችን ይፈጥራል” ሲሉም ገልፀዋል።
“ዕምቅ ሀብታችንን ለኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ዕድገታችን በጥቅም ላይ ለማዋል አብራችሁኝ እንድትጓዙ እጠይቃለሁ፤ የኢትዮጵያ ብልጽግና አይቀሬ ነውም” ብለዋል።
በተያያዘ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በእንጦጦ መንገድ ላይ የሚገኙ ነዋሪዎችና ባለሱቆች ለመንገድ ማስፋፊያ ሥራው ሲሉ፣ በፈቃደኝነት ኑሯቸውን እና ሥራቸውን ከአካባቢው ስላዛወሩ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።
“ለልማት የቀረበውን ጥሪ ተቀብላችሁ፣ በፈቃደኝነት ለጋራ ብልጽግናችን መንገድ ከፍታችኋል፤ መንግስትም ይህንን ላደረጉ ነዋሪዎች በማህበር ተደራጅተው የሚሰሩበትን የተሻለ ቦታ እንደሚያመቻች አረጋግጣለሁ” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።