Fana: At a Speed of Life!

አልሸባብ ያሠበው የሽብር ሴራ በመከላከያ ሰራዊት እና በሶማሌ ክልል ልዩ ሃይል ከሽፏል -ሜ/ጄ ተስፋዬ አያሌው

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአልሸባብ ኃይል ያሠበው የሽብር ሴራ በመከላከያ ሰራዊት እና በሶማሌ ክልል ልዩ ሃይል አባላት መክሸፉን የቀጠናው ኮማንድ ፖስት አስታወቀ፡፡
 
በመከላከያ ህብረት ዘመቻ ዋና መምሪያ የኃይል ሥምሪት መምሪያ ኃላፊ እና የቀጠናው ጊዜያዊ ኮማንድ ፖስት አስተባባሪ ሜጀር ጄኔራል ተስፋዬ አያሌው እንደገለጹት፥ በሶስት አቅጣጫ የሽብር ተግባር ለመፈፀም አስቦ የተንቀሳቀሰው አልሸባብ በመከላከያ ሠራዊት እና በሶማሌ ክልል ልዩ ሃይል ተደምስሷል።
 
በተወሰደው የተቀናጀ እርምጃም በርካታ ቁጥር ያለው የሽብር ቡድኑ ሃይል መማራኩን የተናገሩት ጀኔራል መኮነኑ፥የሽብር ቡድኑ ኤልከሬ በተባለው ቦታ ቀብሮት የነበረው ትጥቅ እና ስንቅ በህብረተሠቡ ጥቆማ መያዙንም አንስተዋል፡፡
 
የፀጥታ ኃይሉ ሠርጎ ለመግባት የሞከረውን የአልሸባብ ኃይል ከኋላ በመቁረጥ በየትኛውም አቅጣጫ መውጣት እንዳይችል አድርጎ ደምስሷል ነው ያሉት።
 
አሁን ላይም ቀጠናውን በማፅዳት እና የተንጠባጠበውን አሸባሪ እየለቀመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
 
በጠረፍ አካባቢ ለወራት ሠው ሲያሠባስብ እና ሲያሠለጥን የቆየው አሸባሪው አልሸባብ ኢትዮጵውያን የውስጥ ችግር አለባቸው በሚል የተሳሳተ አመለካከት ሰርጎ ለመግባት መሞከሩን ነው ያመለከቱት።
 
ከቻለ ከሸኔ ሃይል ጋር በመገናኘት ጥምረት ፈጥሮ ቀጠናውን ሠላም ለማሳጣት አስቦ መንቀሳቀሱንም አብራርተዋል፡፡
 
የተለየ ሀገር ዜግነት ያላቸው ግለሠቦች የሽብር ቡድኑን ሲያሠለጥኑ መቆየታቸውን እና ሀገር ጠል የሆኑ ኢትዮጵያውያኖች ከሽብር ቡድኑ አባላት ጋር መገኘታቸውንም የኮማንድ ፖስቱ አስተባባሪ መናገራቸውን ከመከላከያ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
 
ከፍተኛ ሀገራዊ ስሜት በተንፀባረቀበት እና ፍፁም የበላይነት በታየበት ድል የፀጥታ ሃይሎቻችን ሳይኩራሩ ባለመዘናጋት እና ክፍተት ባለመፍጠር ጥንቃቄ በተሞላበት አግባብ ሁሌም ዝግጁ መሆን እንዳለባቸው ሜጄር ጄኔራል ተስፋዬ አሳስበዋል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.