Fana: At a Speed of Life!

የአረንጓዴ አሻራ ስኬት አገራችን ድንቅ መስራት እንደምትችል ትልቅ ማሳያ ነው – የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር እስከአሁን ከ24 ቢሊየን 2 ሚሊየን በላይ ችግኞች መተከላቸውን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለፀ፡፡

አገልግሎቱ የአረንጓዴ አሻራ ስኬት አገራችን ድንቅ መስራት እንደምትችል ትልቅ ማሳያ ነው ሲል ገልጿል ዛሬ ባወጣው መግለጫ፡፡

የአረንጓዴ አሻራ ፕሮጀክት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሃሳብ አመንጪነት በ2011 ዓ.ም በይፋ ሲጀመር ለአራት ተከታታይ ዓመታት 20 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል የተጀመረ አገራዊ ፕሮጀክት መሆኑን አስታውሷል፡፡

በአጠቃላይ እስከአሁን ድረስ ከ24 ቢሊየን 2 ሚሊየን ችግኝ በላይ መተከሉ ተመላክቷል።

ይህም ከተቀመጠው ግብ በ4 ቢሊየን ችግኝ የበለጠ ነው።

የዚህ በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነው ፕሮጀክት ዓላማ የደን መመናመን አደጋን ለመግታት፣ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ተጽእኖ ለመቋቋም፣ የሚገነቡ ትላልቅ ግድቦችን ከደለል ለመታደግ፣ የተፋሰስና ደን ልማትን ማረጋገጥ ነው ብሏል።

በዚህም ላለፉት ሶስት የክረምት ወቅቶች በተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብሮች ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ እና ስነምህዳራዊ ጠቀሜታዎች መገኘታቸው ተነስቷል።

ለአብነትም በ2013 ዓ.ም በተደረገ ጥናት የኢትዮጵያ የደን ሽፋን 17 በመቶ መድረሱን ጠቅሷል፡፡

ዛፎችን ከመትከል ባሻገር ለምግብነት የሚውሉ የአትክልት እና ፍራፍሬ ችግኞችን በማልማት በምግብ ዋስትና ራሳችንን የመቻል አቅማችንን ማሳደግ እንደሚያስችል እና የህዳሴ ግድብን ጨምሮ ሌሎች ወንዞች በደለል እንዳይሞሉም የአርንጓዴ አሻራ ልማቱ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንደሚያበረክት ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም በመላው ሀገሪቱ ባሉት 120 ሺህ የችግኝ ጣቢያዎች አማካኝነት በርካታ የሥራ እድል የተፈጠረ ሲሆን÷ በዚህ መርሃ ግብር አማካኝነት ችግኝ በዘመቻ መትከል ብቻ ሳይሆን ተንከባክቦ ማሳደግና ለውጤት ማብቃት ትኩረት የሚሻ ጉዳይ እንደሆነ ግንዛቤ ማስፋት መቻሉ ተገልጿል።

ብርድና ዝናብ ሳይበግራቸዉ የራሳቸውን አሻራ ያኖሩትን ሁሉ ኢትዮጵያ ታመሰግናለች ያለው መግለጫው፥ በቀጣይም ለተተከሉ ችግኞች አስፈላጊውን ክብካቤ በማድረግ አገራዊ ግቦቻችን እንዲሳኩ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪውን አቅርቧል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.