Fana: At a Speed of Life!

የድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጠና በሁሉም መስክ ቀልጣፋ ስርዓት የሚገነባበት ነው – ጠ/ሚ ዐቢይ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጠና በሁሉም መስክ ቀለል ያለና ቀልጣፋ ስርዓት የሚገነባበት ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የድሬዳዋን ነጻ የንግድ ቀጠና መርቀው ሲከፍቱ እንደገለጹት÷ የኢትዮጵያን ብልጽግና መሠረት እያጸኑ ለመሄድ መንቃት እና አዳዲስ አሰራር መጀመር ያስፈልጋል፡፡

ነፃ ቀጣናው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ በመጣው አለም አቀፍ የንግድ ትስስር ኢትዮጵያ ተወዳዳሪ እንድትሆን ያስችላታል ነው ያሉት፡፡

እንዲሁም የአገራችንን የወጪ እና ገቢ ንግድ ስርዓት የሚያዘምን እና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ስበት ከፍ የሚያደርግ እንደሆነም ነው ያመለከቱት።

በኢትዮጵያ ባለፉት አመታት በተለይ በግብርና ዘርፍ ትልቅ ውጤት ተገኝቷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ይህ የበለጠ እንዲያድግ ነጻ የንግድ ቀጠናው ወሳኝ ነው ብለዋል።

ከድሬዳዋ በተጨማሪ በሌሎች የሀገሪቱ የንግድ ኮሪደሮችም ነጻ የንግድ ቀጠናው እንደሚስፋፋም አስታውቀዋል።

በተለመደው መንገድ እየተጓዝን የሀገራችንን የኢኮኖሚና የቴክኖሎጂ አቅም ማሳደግ አዳጋች መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህም አዲስና ፈጠራ የታከለባቸው መንገዶችን መከተል ይኖርብናል ብለዋል።

ዓለም በእጅጉ እየተቀየረ ነው፤ በቀድሞ አስተሳሰብ አዲሱን ዓለም ለመቀበል መሞከር ልጆቻችንን በሕጻንነታቸው ባዘልንበት ጫንቃችን በወጣትነታቸው ለማዘል እንደመሞከር ይቆጠራል ሲሉም ተናግረዋል።

እየገነባናቸው ያለት ነፃ የንግድ ቃጣናዎች በፍጥነት እየተለወጠ ወደሚገኘው ዓለም የምንቀላቀልባቸው መንገዶቻችን ናቸው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ።

ዞኖቹ ንግድና ኢንቨስትመንትን ከማቀላጠፍ ባለፈ የቴክኖሎጂ አቅማችንን እንደሚያሳድጉ አልጠራጠርም ሲሉ ገልፀዋል።

በአላዛር ታደለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.