የምክር ቤት አባላት ከመረጣቸው ሕዝብ ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 8 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት ከመረጣቸው ሕዝብ ጋር በጎፋ ዞን ሣውላ ከተማ በልማትና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አካሂደዋል።
በውይይቱ የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ አባልና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ በልጅጌ፣ የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ጌትነት በጋሻው፣ የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባል አቶ ተፈሪ አባተ፣ የጎፋ ዞን ሕዝብ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤና በፌዴሬሽን ምክር ቤት የኦይዳ ሕዝብ ተወካይ አቶ ጠንክር ጠንካ እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎች÷ በዞኑ በሚገኙ መዋቅሮች የሚነሱ የሶዶ-ዲንኬ-ሣውላ-ሸፊቴ መንገድ እና ሌሎች የገጠር መንገድ ተደራሽነት፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ የመብራት አቅርቦትና ተደራሽነት፣ የሣውላ ካምፓስ ወደ ዩኒቨርሲቲ ደረጃ እንዲያድግ ጠይቀዋል።
አቶ ተስፋዬ በልጅጌ በሰጡት ምላሽ÷ ብልጽግና ፓርቲ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በመሆን ትላልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ የኢትዮጵያን ብልጽግና ራዕይ እውን ለማድረግ እየሠራ ይገኛል ብለዋል።
የሶዶ-ሣውላ-ሸፍቴ አስፋልት መንገድ ግንባታ የሀገራዊ ለውጡ ትሩፋት መሆኑን ጠቁመው÷ የተጀመሩ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች በጥራትና በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ አመራሮች ከሕዝቡ ጋር በቅንጅት ሊሠሩ ይገባል ማለታቸውንየዞኑ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
የተጀመሩ የልማት ሥራዎች በተለይ በውሃ፣ መንገድ፣ መብራት፣ ጤና እና ትምህርት በማጠናቀቅ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ለመጀመር ከፌደራል ጀምሮ በየደረጃው ያሉ ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅተው እንደሚሠሩ አመላክተዋል፡፡
አቶ ጠንክር ጠንካ በበኩላቸው÷ በየአካባቢው የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ከፍተኛ ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
አቶ ተፈሪ አባተ እንደገለጹት÷ በጎፋ ዞን ዛላ እና ዑባ ደብረፀሐይ ወረዳዎች በአየር መዛባት ምክንያት በድርቅ የተጎዱ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚደረጉ አስቸኳይ ድጋፎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ።
እነዚህን አካባቢዎች ከዝናብ ጥገኝነት ለማላቀቅ የአካባቢውን አርሶአደሮች በዘላቂነት ተጠቃሚ ለማድረግ በቀጣይ ሳምንት ጥናትን መሠረት በማድረግ የጥልቅ ጉድጓድ ቁፋሮ እንደሚጀመርም ነው የተናገሩት።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እና በምክር ቤቱ የከተማ እና መሠረተ ልማት ቋሚ ኮሚቴ አባል አቶ ጋሽያለው ጋላ÷ የሶዶ-ዲንኬ-ሣውላ-ሸፊቴ መንገድ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ከመቼውም ጊዜ በላይ ተጠናክሮ መንገዱን ለማስጨረስ እየተሠራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
የሶዶ-ዲንኬ-ሳውላ-ሸፊቴ ተቋራጩ ካቀረበው ማነቆዎች በመነሳት በ 2015 በጀት ዓመት የመንገዱ ግንባታ 93 በመቶ እንደሚደርስና ቀሪው 7 በመቶ በ2016 መግቢያ ላይ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ይሆናል ተብሏልል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሕዝብ የተመረጡ ተወካዮች በዓመት ሁለት ጊዜ ውይይት እንዲያደርጉ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት የተደረገ ውይይት መሆኑ ተገልጿል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!