የብልፅግና ፓርቲ የምስጋናና የገቢ መሰባሰቢያ መርሃ ግብር ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የብልፅግና ፓርቲ የምስጋና እና የገቢ መሰባሰቢያ መርሃ ግብር በዛሬው እለት ተካሄደ ።
በሚሊኒዬም አዳራሽ በተካሄደው የምስጋና እና የገቢ መሰባሰቢያ መርሃ ግብር ላይ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትርና የፓርቲው ፕሬዚዳንት ዐቢይ አህመድን ጨምሮ ሚኒስትሮች፣ የክልል ርእሳነ መስተዳድሮች፣ የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች፣ ባለሀብቶች እና የህብረተሰብ ተወካዮች ተገኝተዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይም ከዚህ ቀደም ለብልፅግና ፓርቲ በተለያየ መልኩ ድጋፍ ላደረጉ አካላት ምስጋና ቀርቦላቸዋል።
በተጨማሪም በመድረኩ ላይ ለፓርቲው ከ300 ሺህ ብር አንስቶ የተለያየ መጠን ያለው ገቢም ተሰብስቧል።
በመድረኩ ላይ ፓርቲውን በመወከል ምስጋና ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከአርሶ አደሮች እስከ ከፍተኛ ባለሀብቶች ድረስ ለፓርቲው የገንዘብ ድጋፍ ማድጋቸውን በማንሳት አመስግነዋል።
“ብልፅግና ከእናንተ የወሰደውን ሀብት ካለምንም መባከን ከመንግስት መጠቅም የሚገባውን እና ሲጠቀም የነበረውን አካሄድ አስተካክሎ ፓርቲና መንግስትን በለየ መልኩ ሀብቱን ትክክለኛ ቦታ ላይ በማዋል ዛሬ የሰጣችሁት በመደመር ብቻ ሳይሆን በመባዛት በሚቀጥለው ምርጫ አራት እጥፍ መስጠት እንድትችሉ የሚያበቃ ስራ የሚሰራ ይሆናል” ብለዋል።
“ካለስስት አጋር የሆናችሁን መርከቧመድረስ ከሚገባት ቦታ አድረሰን እናኮራችኋለን ብለዋል” በመልዕክታቸው።
“መነሻችን ልማት መድረሻችን ብልጽግና ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የማንፈልገውን ድህነት በስራ እናጠፋለንም ብለዋል።
ብልፅግና ፓርቲ ባለሀብቶች ደጋፊ ብቻ ሳይሆን አባላት፣ አመራር እና መሪዎች ሊሆኑ ይገባል የሚል አቋም መያዙንም አስታውቀዋል።
የፓርቲው ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል እና የኢፌዴሪ የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል፥ በተለያየ መልኩ ለብልፅግና ፓርቲ ድጋፍ ላደረጉ አካላት ምስጋና እና እውቅናን ሰጥተዋል።
ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል አክለውም፥ እስካሁን በተሰራው የገቢ ማሰባሰብ ስራም 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ማሰባሰብ መቻሉንም በመድረኩ ላይ ይፋ አድርገዋል።