ዓለምአቀፋዊ ዜና

የአሜሪካ ኮንግረስ አባላት ለጉብኝት ታይዋን ገቡ

By Alemayehu Geremew

August 14, 2022

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በዛሬው ዕለት የአሜሪካ ኮንግረስ ልዑካን ቡድን ለሁለት ቀናት ጉብኝት ታይዋን መግባታቸው ተገለጸ።

የአሜሪካ ኮንግረስ ሕግ አውጪ አባላት ታይዋን የገቡት፥ የአሜሬካ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ናንሲ ፔሎሲ ታይዋንን ከጎበኙ ሁለት ሣምንታት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

በታይዋን ዋና ከተማ ታይፔይ የሚደረገውን የልዑካኑን ጉብኝት ይፋ ያደረገው ደሴቲቱን እንደ ራስ-ገዝ አስተዳደር ቆጥሮ እንደ አሜሪካ ኤምባሲ የሚንቀሳቀስ ተቋም ነው ተብሏል፡፡

እንደ ተቋሙ መረጃ ዴሞክራቱ የማሳቹሴትስ ሴናተር ኤድ ማርኬይ ልዑካን ቡድኑን መርተው ታይዋን ገብተዋል።

በጉብኝቱ የዴሞክራቶቹ ተወካይ የሆኑት ÷ ጆን ጋራሜንዲ እና አለን ሎዌንታል ከካሊፎርኒያ እንዲሁም ዶን ቤየር ከቨርጂኒያ ከቡድን መሪው ጋር በታይፔይ ተገኝተዋልም ነው የተባለው፡፡

በተጨማሪ ከሪፐብሊካኑ ወገን ደግሞ አሙአ አማታ ኮልማን ራዴዋገን ከሳሞአ በመርሐ-ግብሩ ላይ ተሳታፊ መሆናቸውን አር ቲ ዘግቧል፡፡

ልዑካን ቡድኑ ከታይዋን መሪዎች ጋር በቀጣይ በሚኖራቸው ግንኙነት ዙሪያ እንደሚመክሩ ኢንስቲቲዩቱ ገልጿል።

በቀጠናዊ ደኅንነት፣ በንግድ እና ኢንቨስትመንት፣ በዓለምአቀፍ የአቅርቦት ሰንሰለቶች፣ በዓየር ንብረት ለውጥ እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ እንደሚወያዩም ነው የተመለከተው፡፡