Fana: At a Speed of Life!

የባህር ዳር እና የግልገል በለስ ከተሞች በጋራ ለመልማት ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የባህር ዳር እና የግልገል በለስ ከተሞች በጋራ ለመልማት የሚያስችል ሰነድ ተፈራረሙ፡፡

የሁለቱ እህትማማች ከተሞች የጋራ የልማት መድረክ በግልገል በለስ ከተማ የሁለቱም ከተሞች ፣ የአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞንና የመተከል ዞን ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ተካሂዷል።
የስምምነቱ ዋና አላማ በሁለቱ ከተሞች በሚኖሩ ህዝቦች መካከል አንድነትን ለማጠናከር እና የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መዳረሻ የሆነችውን ግልገል በለስ ከተማ እድገት ለማስቀጠል ታሳቢ ያደረገ ነው ተብሏል፡፡

የባህር ዳር ከተማ ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ÷በቀጣይ ግልገል በለስ ከተማ ለጎብኚዎች ምቹና ሳቢ እንድትሆን በተለያዩ ዘርፎች የከተማዋን ችግር በጋራ ለመፍታት በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የግልገል በለስ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ ኑራ ሳለህ በበኩላቸው÷ የተዘራውን የጥላቻ ዘር ነቅለን ችግኞችን በመትከል ውብና ምቹ አካባቢን መፍጠር ይገባል ብለዋል ።

በእህትማማች ከተሞች የአረንጓዴ አሻራ ፓርክ ላይ የተተከሉ ችግኞችን ለታለመላቸው ዓላማ ለማዋል በትኩረት መሰራት እንዳለበት ተናግረዋል።

ከተማ አስተዳደሩ ለባህር ዳር ከተማ አስተዳደር እና ለአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን የምስጋና ምስክር ወረቀት ማበርከቱን ከመተከል ዞን ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.