Fana: At a Speed of Life!

አቶ አሻድሊ ሃሰን በሕገ ወጥ የወርቅ አዘዋዋሪዎች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ አስታወቁ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የማዕድን ግብረ ኃይል ከወርቅ ማዕድን ምርት ጋር በተያያዘ በሕገ ወጥ መንገድ ሲያዘዋውሩ በተገኙ አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሃሰን እንደገለጹት÷ የሚመረተውን የወርቅ መጠን ለማሳደግ ባለ ድርሻ አካላት ትኩረት ሰጥተው መረባረብ ይገባቸዋል፡፡
የሚመረተውን ወርቅ በሕጋዊ መንገድ ለብሔራዊ ባንክ እንዲገባ በማድረግ ረገድም ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
ወርቅ እንደኢትዮጵያ ላሉ ሀገራት ከነዳጅ ያልተናነሰ የገቢ ምንጭ መሆኑን ጠቁመው÷ በሕገ ወጥ መንገድ የሚያዘዋውሩ አካላት በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ በደል እየፈፀሙ እንደሆነ ተገንዝበው ከዚህ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል፡፡
በክልሉ የሚመረተውንና ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባውን የወርቅ መጠን ለማሳደግ የተለየ ጥረት ከማድረግ ጎን ለጎን ሕገ ወጦችን መስመር ለማስያዝ በትኩረት ይሠራል መባሉን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት የርዕሰ-መስተዳድርና ካቢኔ ጉዳዮች ጽህፈት ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡
በ2014 ዓ.ም ከ2 ሺህ 315 ኪሎ ግራም ወይም 23 ኩንታል በላይ ወርቅ በልዩ አነስተኛ እና በባህላዊ ወርቅ አምራቾች በኩል ተመርቶ ለብሔራዊ ባንክ ገቢ መደረጉን አስታውሰዋል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.