በጃፓን ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ ላደረጉ አካላት ምስጋና ቀረበ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ ላደረጉ አካላት የምስጋና ዝግጅት እና የኢትዮጵያ ባህል ማስተዋወቂያ መድረክ በጃፓን ካናጋዋ ግዛት በማቺዳ ከተማ ተካሄደ።
በዝግጅቱ በክብር እንግድነት የተገኙት አምባሳደር ተፈራ ደርበው÷ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛው የውሃ ሙሌት እንዲጠናቀቅና የሁለተኛው ተርባይን አገልግሎት መስጠት እንዲጀምር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
አምባሳደር ተፈራ በሦስተኛው ዙር ይግድቡ የውሃ ሙሌት መጠናቅ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፥ ስለግድቡ ግንባታ ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅም እና የተፋሰሱ ሀገሮች ሚና ጋር በተያያዘ ገለፃ አድርገዋል።
የባህል ማስተዋወቂያ መድረኩ የሁለቱን ሀገራት ጠንካራ ግንኙነት ይበልጥ የሚያስተሳስር ነው ብለዋል አምባሳደሩ፡፡
በባህል ማስተዋወቂያ ፕሮግራሙ ላይ የኢትዮጵያ ቡና ባህላዊ አቀራረብ፣ የተለያዩ ባህላዊ ምግቦች እና መጠጦች መቅረባቸውንም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በባህል ዝግጅቱ በኢትዮጵያ የቀድሞ የጃፓን አምባሳደር ዳይሱኬ ማትሱናጋን ጨምሮ በጃፓን የሚኖሩ የኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች መገኘታቸው ተገልጿል።