የሀገር ውስጥ ዜና

አቶ ደመቀ መኮንን ከእንግሊዝ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጋር ተወያዩ

By Alemayehu Geremew

August 17, 2022

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 11 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከእንግሊዝ የአፍሪካ ቀንድ እና ቀይ ባህር ልዩ መልዕክተኛ ሳራ ሞንትጎመሪ ጋር ተወያዩ።

በውይይቱም እንግሊዝ ከኢትዮጵያ ጋር ስላላት የረጅም ጊዜ ወዳጅነት አስታውሰው፥ በእንግሊዝ መንግስት በኩል እየቀረበ ላለው ዘርፈ ብዙ ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ የሰሜኑ ክፍል የተፈጠረውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መንግስት ቁርጠኛ መሆኑን በመጥቀስም፥ ችግሩን ለመፍታት በመንግስት በኩል እየተወሰዱ ስላሉ ዝርዝር ጉዳዮች ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

የእንግሊዝ የአፍሪካ ቀንድ እና ቀይ ባህር ልዩ መልዕክተኛ ሳራ ሞንትጎመሪ በበኩላቸው የመጀመሪያቸው በሆነው ጉዞ ብዙ ነገሮች ላይ ግንዛቤ እንዳገኙ ጠቅሰዋል።

በሃላፊነታቸው በሀገራቱ መካከል ያለው የረጅም ጊዜ ወዳጅነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የድርሻቸውን እንደሚወጡ መናገራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት መረጃ ያመላክታል።

የሰላም ሂደቱን ለመደገፍም ዝግጁ መሆናቸው አስረድተዋል።