የመከላከያ ሚኒስቴር ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ዜጎች የመኖሪያ ሕንፃ ግንባታ አስጀመረ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌ.ዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው 64 አባዎራዎች ተጠቃሚ የሚሆኑበት የG+4 መኖሪያ ሕንፃ ግንባታ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ አስጀምሯል።
የመከላከያ ሚኒስትር አብርሃም በላይ በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት÷የመከላከያ ሠራዊት የአገሩን ዳር ድንበር ለማስከበር እየከፈለ ካለው መስዋዕትነት በተጨማሪ ሕዝብ በችግር ሲጠቃ ፈጥኖ በመድረስ አለኝታነቱን እያሳየ ነው ብለዋል፡፡
ሚኒስቴሩ በዛሬው ዕለት ግንባታቸው የተጀመሩ ቤቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ በማጠናቀቅ ለነዋሪዎች እንደሚያስረክብም ተናግረዋል፡፡
በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መለሰ አለሙ በበኩላቸው÷ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የህብረተሰቡን ችግር በማቃለል ኃላፊነቱን ለመወጣት እያደረገ ያለው ጥረት ሕዝባዊነቱን የበለጠ የሚያጎላ ነው ብለዋል፡፡
አክለውም “በተባበረ ክንድ ችግሮችን ከስር እየነቀልን የኢትዮጵያን ከፍታ እናረጋግጣለን” ማለታቸውን ከአዲስ አበባ ከተማ የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡