የሀገር ውስጥ ዜና

የሰዎች ህገ ወጥ ዝውውርን ለመከላከል የተሰሩ ተግባራትን የሚገመግም መድረክ እየተካሄደ ነው

By Amele Demsew

August 18, 2022

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሰው መነገድ፣ ሰውን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር እና በህገ ወጥ መንገድ ለስራ ወደ ውጭ አገር የመላክ ወንጀልን ለመከላከል የተከናወኑ ተግባራትን የሚገመግም መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡

መድረኩን ያዘጋጀው በሰው መነገድ፣ በህገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገርና ለሥራ ወደ ውጭ ሀገር የመላክ ወንጀሎችን ለመከላከልና መቆጣጠር የተቋቋመው ብሔራዊ ምክር ቤት መሆኑ ተገልጿል።

ብሔራዊ ምክር ቤቱ ባካሄደው በዚሁ ዓመታዊ ስብሰባው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንን ጨምሮ የተለያዩ ጥሪ የተደረገላቸው ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

በመድረኩ ላይ ባለድርሻ ተቋማት የሥራ ክንውናቸውን ማቅረባቸውም ተገልጿል፡፡

በሰው የመነገድ፣ ሰውን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር እና በህገወጥ መንገድ ለስራ ወደ ውጭ አገር መላክ ወንጀሎች በዜጎች አካል፣ ህይወት እና ደህንነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ እና ለሰብአዊ መብት ጥሰት እያገለጡ የሚገኙ ወንጀሎች መሆናቸው ይታወቃል።

በአዳነች አበበ