Fana: At a Speed of Life!

የ33 ነጥብ 5 ሜትር ፀጉር ባለቤቷ የፍሎሪዳ እመቤት

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የፍሎሪዳዋ ክሌርሞንት ነዋሪ አሻ ማንዴላ ባለ ረጅም ፀጉሯ እመቤት በመባል ስማቸውን በዓለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ አስፍረዋል።

የ60 አመቷ ወይዘሮ ፀጉራቸው 33 ነጥብ 5 ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን፥ ፀጉራቸውን ከትሪዳድና ቶቤጎ ወደ አሜሪካ በመጡበት የዛሬ 40 አመት ማሳደግ መጀመራቸውን ይናገራሉ።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ፀጉራቸው እድገቱን የቀጠለ ሲሆን፥ በፈረንጆቹ 2009 ፀጉራቸው 5 ነጥብ 8 ሜትር በመያዝ ባለ ረጅም ፀጉር የሚለውን ስያሜ አግኝተው ነበር፡፡

ማንዴላ ብዙ ጊዜ ፀጉራቸውን በጨርቅ በመጠቅለል መሬት ላይ እንዳይጎተት እና የፀጉራቸው ጫፎች እንዳይወጠሩ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚያደርጉ ይገልጻሉ።

ከዚህ ባለፈም በመኝታቸው ወቅት ፀጉራቸውን በመጠቅለል እና በአነስተኛ ቅርጫት በማስቀመጥ አቅፈውት እንደሚተኙም ነው የሚናገሩት።

ፀጉራቸውን እንደሚወዱት የሚናገሩት አሻ ማንዴላ “ድሬድ” የሚለውን ስያሜ እንደማይወዱት እና ፀጉራቸውን “የእኔ ዘውድ” ወይም “ኮብራ” በሚል ስያሜ እንደሚጠሩትም ለጊነስ ቡክ ኦፍ ሪከርድስ ተናግረዋል።

አያይዘውም ፀጉራቸውን የመቆረጥ ፍላጎት እንደሌላቸው እና ከዚህ በተሻለ የማሳደግ ፍላጎት እንዳላቸውም አስረድተዋል።

የማንዴላ ባለቤት የሆኑት ኢማኑኤል ቼጌ ከናይሮቢ ኬንያ የመጡ የፀጉር ስራ ባለሙያ ሲሆኑ፥ የማንዴላን ፀጉር በመንከባከብ ብዙ ጊዜ እንደሚያሳልፉ ገልጸዋል፡፡

እንደ ቼጌ ገለፃ የማንዴላ ፀጉር በሳምንት አንድ ጊዜ የሚታጠብ ሲሆን እስከ ስድስት ጠርሙስ ሻምፖ የሚያስፈልገው ሲሆን፥ ለመድረቅ ደግሞ ሁለት ቀናት ይወስዳል።

ዘገባው የዩናይትድ ፕረስ ኢንተርናሽናል ነው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.