Fana: At a Speed of Life!

17ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል “ሕብረ ብሔራዊ አንድነታችን ለዘላቂ ሰላማችን!” በሚል መሪ ቃል ይከበራል

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) 17ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል “ሕብረ ብሔራዊ አንድነታችን ለዘላቂ ሰላማችን!” በሚል መሪ ቃል እንደሚከበር የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስታወቀ፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር፥ በዓሉ በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነትና በሲዳማ ክልል አስተናጋጅነት በድምቀት እንደሚከበር ነው ያስታወቁት፡፡

በዓሉ ሕዝቦች እኩልነታቸውን፣ አንድነታቸውንና ወንድማማችነታቸውን የሚያጠናክሩበት፥ ባህላዊ እሴቶቻቸውን የሚያንፀባርቁበት፣ ማንነታቸው በሚገባ ያልታወቀላቸው ሕዝቦች እሴቶቻቸውን በአደባባይ የሚያስተዋውቁበት እንደሚሆንም ገልጸዋል፡፡

አክለውም ይህ በዓል ሕገ መንግሥቱ የጸደቀበትን ቀን ምክንያት በማድረግ የሚከበር ገልጸው፥ መላው የሕብረተሰብ ክፍል በተለይም ወጣቱ ትውልድ ስለሀገሩ ሀገረ መንግሥት ግንባታ፣ ስለሕገ መንግሥቱ፣ ስለታሪኩ እና ባህሉ ተገንዝቦ በማንነቱ እንዲኮራ የማድረግ ዓላማ እንዳለውም ነው የጠቆሙት፡፡

አያይዘውም ይህ በዓል አንዳንዶች እንደሚሉት የባህል ውዝዋዜና ጭፈራ የሚታይበት ብቻ ሳይሆን፥ ስለሕገ መንግሥቱ እሳቤዎች ሰፊ የአስተምህሮ ሥራ በመሥራት ሁለንተናዊ ግንዛቤ ለማስጨበጥ፣ የዜጎችን ምክንያታዊ አስተሳሰብ ለማዳበርና አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ ለመገንባት የሚያስችል መደላድል ለመፍጠር እንደሚያግዝ አስረድተዋል፡፡

ወደፊት ይህን በዓል ከፍ ባለ ደረጃ የኢትዮጵያ ቀን አድርጎ ማክበር እንደሚቻልም ጠቁመዋል፡፡

በዓሉ ለአንድ ቀን ብቻ የሚከበር ሳይሆን ከአሁኑ ጀምሮ በፌዴራልና በክልሎች የሚገኙ ተቋማትን በየደረጃው በማስተባበር በተለያዩ ሁነቶች በድምቀት ሊከበር ይገባል ሲሉም ነው ያሳሰቡት፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.