Fana: At a Speed of Life!

በደቡብ ክልል የሚነሱ የመዋቅር ጥያቄዎች በሰላማዊ መንገድ ብቻ የሚፈፀሙ ይሆናል- የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የክልልነት፣ የዞን እና የልዩ ወረዳ እንሁን የሚሉ አስተዳደርን መሰረት ያደረጉ ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ የሚያገኙት በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንደሚሆን መንግስት ፅኑ እምነት አለው ሲሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ ተናገሩ፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ዛሬ ለሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን በሰጠው መግለጫ ከአስተዳደር ውሳኔዎች ጋር በተያያዘ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡

ሚኒስትሩ የህግ መሰረት በሌለውና በኢመደበኛ የተደራጁ ታጣቂዎች በመታገዝ ጥያቄዎችን በጉልበት ለመፍታት የሚደረግ ጥረት ብዙ ዋጋ ሲያስከፍል የቆየ እንደሆነና አሁንም ሊያስከፍል እንደሚችል አስጠንቅቀዋል፡፡

በክልሉ የሚነሱ ጥያቄዎች በህገመንግስቱ የተቀመጡ መርሆዎችን በመከተል ምላሾችን በሰከነ መንገድ መጠበቅ እንደሚገባ የገለፁት ሚኒስትሩ፥ የግጭት ነጋዴዎች እና የጥቂት ፖለቲከኞች የጥቅም ማስፈፀሚያ እንዳይሆኑም መጠንቀቅ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ጥያቄዎች የህዝብን ፍላጎትና ጥቅም ባስከበረ መልኩ በህጋዊ መንገድ ቀርበው ምላሽ ማግኘት እንደሚችሉም ነው የገለፁት፡፡

ለማሳያነትም ከሰሞኑ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በደቡብ ክልል ስር የነበሩ 6 ዞኖችና 5 ልዩ ወረዳዎች በአንድ ክልል እንደ አዲስ እንዲደራጁ የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ ተቀብሎ ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ መወሰኑን ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም የወላይታ፣ ጋሞ፣ ጎፋ፣ ጌዴኦ፣ ኮንሶ እና ደቡብ ኦሞ ዞኖች እንዲሁም፥ ደራሼ፣ አማሮ፣ ቡርጂ፣ አሌ እና ባስኬቶ ልዩ ወረዳዎች አንድ ላይ ሆነው አዲስ ክልል ለማቋቋም የምርጫ ቦርድ ቀጣይ በሚያስቀምጠው አቅጣጫ መሰረት ህዝበ ውሳኔ የሚያካሂዱ እንደሚሆንም ገልፀዋል፡፡

ቀሪዎቹ የሀዲያ፣ ሀላባ፣ ከንባታ ጠንባሮ፣ ጉራጌ እና ስልጤ ዞኖች እና የየም ልዩ ወረዳ በነባሩ የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል አንድ ላይ እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡

ሂደቱ የህዝቦችን ያደሩ እና የቆዩ ችግሮች በመፍታት እውነተኛ ፌዴራላዊ ስርዓት የመገንባት አቅጣጫ ስኬታማነትንም የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ እና የፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን የአስተዳደር ወሰን ማካለል ጉዳይ በተመለከተም አብራርተዋል።

በማብራሪያቸው፥ ውሳኔው የከተሞችን ተፈጥሯዊ እድገት በእቅድ መምራት በሚያስችል መልኩ በጥልቅ ጥናት ላይ  ተመስርቶ የተፈፀመ መሆኑን አስታውቀዋል።

በዚህ ውሳኔ ውስጥ በሁለቱም ወገን ግማሽ ሚሊየን ህዝብ ተሳታፊ መሆኑን ነው ያመለከቱት።

ውሳኔው ዘላቂ ትስስር፣ ሰላም እና የጋራ ተጠቃሚነትን በአስተማማኝ ሁኔታም የሚመልስ ነው ብለዋል።

ጉዳዩን ለአላስፈላጊ  የፖለቲካ ፍጆታ መጠቀም  የሚፈልጉ አካላት፥ ውሳኔው ህግን መሰረት አድርጎ  የተዘጋጀ በመሆኑ ሀሳባቸው እንደማይሳካ አውቀው ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ አሳስበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.