Fana: At a Speed of Life!

ከ48 ሺህ በላይ ለሆኑ ወጣቶች ቋሚ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል- የደቡብ ምዕራብ ክልል

አዲአበባ፣ ነሐሴ 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ከ48 ሺህ በላይ ለሆኑ ወጣቶች ቋሚ የሥራ ዕድል መፈጠሩን ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ ተናገሩ፡፡
የክልሉ ም/ቤት ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትና ከክልሉ አስፈፃሚ አካላት ጋር በመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች እና ምላሽ ባገኙ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ በውይይቱ ላይ እንደገለጹት÷ በሰላምና ጸጥታ፣ በሥራ አጥነት ዘርፍ፣ በኑሮ ውድነት ፣ በድርቅ ምክንያት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ በማቋቋም ረገድ እንዲሁም በአርብቶ አደሩ አካባቢ በቅንጅት እየተሠራ ነው፡፡
በሕዝብ ሲነሱ ከነበሩ ጥያቄዎች መካከል የመሠረተ ልማት ችግሮች መሆናቸውን ጠቁመው÷ ለእዚህም ቅድሚያ ተሰጥቶ የመንገድና የድልድይ ግንባታ ሥራዎች ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
11 የጤና ተቋማትና የቴክኒክ እና ሙያ ትምህርት ስልጠና ማዕከላት አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉንም ነው የገለጹት፡፡
ግብርውን ውጤታማ ለማድረግና ወደ ሜካናይዜሽን ሥራ ለመግባት የ15 ትራክተሮች ግዢ መፈጸሙንም ጠቁመዋል፡፡
ከ48 ሺህ በላይ ለሆኑ ወጣቶች ቋሚ የሥራ ዕድል መፈጠሩን ጠቅሰው፥ የሥራ ዕድል ፈጠራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡
የክልሉን ገቢ ከማሳደግ አንጻር ልዩ ትኩረት በመስጠት የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም መናገራቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡
ለክልሉ የጸጥታ ሥራዎች ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት በመሰጠቱ አንጻራዊ ሰላም ማምጣት መቻሉንም ነው ምክትል ርዕሰ መስተዳድር የተናገሩት።
የክልሉ ም/ቤት ዋና አፈ ጉባዔ አቶ ወንድሙ ኩርታ በሰጡት አስተያየት÷ በክልሉ እና በሕዝብ ተወካዮች አማካይነት የሕዝብን ጥያቄ ለመመለስ የተሄደበት መንገድ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚመለከተው አካል ትኩረት እንዲሰጥበት ጠይቀዋል፡፡
ለዚህም ተቀናጅቶ መሥራት እንደሚገባ አመልክተው፥ የፌደራል ተቋማት ለክልሉ የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዲያጠናክሩም ጠቁመዋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.