Fana: At a Speed of Life!

በጦርነቱ ጉዳት ከደረሰባቸው 536 የጤና ተቋማት 463ቱ አገልግሎት መስጠት መጀመራቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሸባሪው የሕወሓት ወረራ በአፋርና አማራ ክልሎች ጉዳት ከደረሰባቸው 536 ጤና ተቋማት ውስጥ 463 የሚሆኑት አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ከዚህ ውስጥ 319 ጤና ተቋማት በከፊል አገልግሎት የጀመሩና ወደ ተሟላ አገልግሎት ለመመለስ ተጨማሪ ሥራ የሚጠይቁ መሆናቸውንም ተጠቁሟል፡፡

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ እንደገለጹት÷ በአሸባሪው የሕወሓት ወረራ በአፋርና አማራ ክልሎች ጉዳት ከደረሰባቸው 536 ጤና ተቋማት ውስጥ 463 የሚሆኑት አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፡፡

ከዚህ ውስጥ 319 ጤና ተቋማት በከፊል አገልግሎት የጀመሩና ወደ ተሟላ አገልግሎት ለመመለስ ተጨማሪ ሥራ የሚጠይቁ መሆናቸውን ነው የገለጹት፡፡

በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በተከሰተው ጦርነት ጉዳት ከደረሰባቸው ተቋማት ውስጥ የጤና ተቋማት ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛሉ ያሉት ሚኒስትሯ÷ ለዚህ ምላሽ ለመስጠት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተለያዩ የድንገተኛ ምላሽ ሥራዎችን ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ሲሠራ ቆይቷል ብለዋል፡፡

ይህን ለማስተግበር እቅድ ተዘጋጅቶ እንደ ሴክተርና ከሌሎችም ሴክተሮች ጋር በገንዘብ ሚኒስቴር በሚመራ የተጀመሩ የመልሶ ግንባታ ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸውን ጠቁመዋል፡፡

በአማራ ክልል ከተጎዱት 40 ሆስፒታሎችና 453 ጤና ጣቢያዎች 10 ሆስፒታሎችና 134 ጤና ጣቢያዎች ወደ ሙሉ አገልግሎት መመለሳቸውን ጠቅሰው÷ 25 ሆስፒታሎችና 273 ጤና ጣቢያዎች ደግሞ ከፊል አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም በክልሉ በርካታ ጤና ኬላዎች በመልሶ ግንባታ ወደ ሥራ መግባታቸውን አስታውሰው፤ አምስት ሆስፒታሎች እና 46 ጤና ጣቢያዎች አሁንም ድረስ አገልግሎት መስጠት እንዳልቻሉ ገልጸዋል፡፡

በአፋር ክልል ጉዳት ከደረሰባቸው ሁለት ሆስፒታሎችና 41 ጤና ጣቢያዎችም አንድ ሆስፒታልና 20 ጤና ጣቢያዎች ታድሰው በከፊል አገልግሎት መጀመራቸውን ጠቁመው÷ አንድ ሆስፒታልና 21 ጤና ጣቢያዎች እስካሁን ወደ ሥራ መመለስ አለመቻላቸውን አንስተዋል፡፡

በሁለቱም ክልሎች ወደ ሥራ ያልገቡ ቀሪዎችን ተቋማት ወደ ሥራ ለመመለስ የጸጥታ ችግር እንቅፋት መሆኑን መግለጻቸውንም ኢፕድ ዘግቧል፡፡

ከክልል ጤና ቢሮዎች፣ ከፌዴራል ሆስፒታሎች፣ ኤምባሲዎች፣ ከልማት አጋር ድርጅቶች፣ ዳያስፖራዎችና የኢትዮጵያ ወዳጆች በመተባበር በተሠራው ሥራ መሠረታዊና ሕይወት አድን የሆኑ ጤና አገልግሎቶች በግጭቱ በተጎዱ ጤና ተቋማት ውስጥ ማስጀመር መቻሉንም አብራርተዋል፡፡

እስካሁን ድረስ ከባለድርሻ አካላት በግብአት፣ በመሳሪያ በገንዘብ 600 ሚሊየን ብር የሚገመት ሃብት መሰብሰቡንም ጠቁመዋል፡፡

ዶክተር ሊያ እስካሁን ድረስ በግለሰብና ተቋም ደረጃ እገዛ ላደረጉ ባለድርሻ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡

 

በርካታ ጤና ተቋማት ወደ ሥራ መመለሳቸው አበረታች ቢሆንም ሁሉም ተቋማት የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ ከፍተኛ ሥራ ስለሚጠይቅ አሁንም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.