Fana: At a Speed of Life!

ህጻናት የተሟላ አእምሯዊና ስነልቦናዊ እድገት እንዲኖራቸው መጫወቻ ቦታዎችን ማዘጋጀት ያስፈልጋል- ከንቲባ አዳነች

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ልጆች የተሟላ አእምሯዊና ስነልቦናዊ እድገት እንዲኖራቸው የተሟሉ መጫወቻ ቦታዎችን ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
 
የቀዳማይ ልጅነት እድገትና እንክብካቤ ፕሮግራም በአዲስ አበባ በተሟላ ሁኔታ ተግባራዊ እንዲደረግ የሚያስችል ውሳኔ ተወስኖ የህፃናትን ሁለንተናዊ እድገት የሚያጎለብቱ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑ ይታወቃል፡፡
 
በፕሮግራሙ ከተካተቱት ስራዎች የህፃናት አካላዊ እንቅስቃሴ እና መዝናኛ ስፍራዎችን ማዘጋጀት አንዱ በመሆኑ ተጠቁሟል፡፡
 
ለዚህም የከተማው አስተዳደሩ አዲስ የተገነባውንና ዘመናዊውን ከኡራኤል-ወሎሰፈር የሚወስደውን የ1 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ እሁድ እሁድ ከመኪና ነፃ ቀን ለህፃናት አካላዊ እንቅስቃሴ በቋሚነት ዝግ እንዲሆን ማድረጉ ተገልጿል፡፡
 
እንቅስቃሴውን ያስጀመሩት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ÷ ህፃናት ስለሀገራቸው እያወቁ እንዲያድጉ እና አእምሯዊና ስነልቦናዊ እድገት እንዲኖራቸው የተሟሉ መጫወቻ ቦታችዎን ማዘጋጀት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
 
ለሁሉም ልጆች የምትመች አዲስ አበባን እንገነባለን ያሉት ከንቲባዋ÷በዚህ ፕሮግራም ላይ ጎዳና ላይ የሚኖሩ ልጆችን ጨምሮ ሁሉም የከተማዋ ህጻናት የሚሳተፉ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
 
በዚህ ፕሮግራም 500 ባለሙያዎች በአዲስ አበባ አስተዳደር ተቀጥረው ወደ እያንዳንዱ ቤተሰብ በመሄድ ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርጉም ከንቲባ አዳነች አስታውቀዋል፡፡
 
የአዲስ አበባ ቀዳማይ ልጅነት እንክብካቤና ድጋፍ ፕሮግራም አስተባባሪ ዶክተር ታቦር ገብረመድህን በበኩላቸው÷ፕሮግራሙ ልጆች የተሟላ ስነልቦናዊና አካላዊ እድገት እንዲኖራቸው እንዲሁም በደስታ ተጫውተው እንዲያድጉ ለማድረግ ያለመ መሆኑን አውስተዋል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.