ከፍተኛ ሙቀት እና ድርቅ የአውሮፓ ፈተና ሆኗል
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአውሮፓ የተከሰተው ከፍተኛ የሙቀት ማዕበል እና ያስከተለው ድርቅ በአህጉሪቱ ከባድ የኢኮኖሚ ቀውስ እያስከተለ ነው ተባለ፡፡
አብዛኛዎቹ የአውሮፓ ሀገራት በተለይም የደቡብ፣ የምዕራብ እና የማዕከላዊ አውሮፓ ክፍል በሙቀት ማዕበሉ በከፍተኛ ሁኔታ መመታቱን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
ከፍተኛ ሙቀቱን ተከትሎ በአውሮፓ የተከሰተው ድርቅ በ500 አመታት ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ነው ተብሏል፡፡
በሙቀቱ እና በድርቅ ሳቢያም በአውሮፓ የግብርና ምርቶች ላይ ከፍተኛ የምርት መቀነስ ማስከተሉን የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን የጋራ ምርምር ማዕከል ያወጣው መረጃ ያመላክታል፡፡
እንደ ማዕከሉ መረጃ ከአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ውስጥ 47 በመቶዎቹ የድርቅ ስጋት የተደነቀነባቸው ሲሆን 17 በመቶ ያክሉ ደግሞ የድርቅ አደጋ አንዣቦባቸዋል።
ድርቁ በተለይ በአፈር ለምነት ላይ ያስከተለው ጉዳት በአውሮፓ ቀጣይ የእርሻ ወቅቶች በግብርና ምርት እና ምርታማነት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ እንደሚያስከትል የእንግሊዙ ጀምስ ሀተን ኢንስቲትዩት ከፍተኛ ተመራማሪ ማይክ ሪቪንግተን ተናግረዋል፡፡
ተመራማሪው እንዳሉት በአንዳንድ አካባቢዎች የአፈር ለምነቱን እንደገና ለመመለስ አዳጋች ይሆናል ፡፡
የተፈጥሮ ሚዛን መዛባት ፣ የወንዞች እና ሃይቆች የውሃ መጠን በከፍተኛ መጠን መቀነስ ብሎም መድረቅ፣ የአፈር ለምነትን መቀነስ እና ሰደድ የሙቀት መጨመሩና ድርቁ ያስከተሏቸው ጉዳቶች መሆናቸውንም ነው ተመራማሪው የሚናገሩት።
በኔዘርላንድስ በአፈር ውስጥ ያለው የጨው መጠን በከፍተኛ መጠን እየጨመረ ሲሆን፥ የውሃ አካላት መበከል፣ ከፍተኛ ሙቀትና መድረቅም የአሳ ሀብት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን የሃገሪቱ የዜና አውታሮች ዘግበዋል።
በሐንጋሪ በአንድ ወር ብቻ በገበሬዎች ላይ የደረሰው ጉዳት ባለፉት አስር አመታት ከደረሰው ጉዳት በእጥፍ የሚበልጥ መሆኑን የሀገሪቱ ግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል።
የሃይል አቅርቦትም ሌላኛው የሀገራቱ ፈተና ሲሆን፥ ከዚህ ጋር ተያይዞ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ጣቢያዎች፣ የኒውክሌር ጣቢያዎች እና የንፋስ ሃይል ማመንጫዎች ላይ የምርት መቀነስ ተስተውሏል ነው የተባለው።
ሙቀቱ ባስከተለው ሰደድ እሳትም በአውሮፓ 660 ሺህ ሄክታር ደን ሲቃጠል፥ በግሪክ፣ በፈረንሳይ፣ በጣሊያን እና በሃንጋሪ ያለው የአየር ንብረት የወይራ ዘይት፣ ወይን፣ በቆሎ እና የእንስሳት መኖ ምርቶች ላይ ከፍተኛ የምርት መቀነስ እንዳያስከትልም ስጋት ፈጥሯል ነው የተባለው፡፡
በውሃ አካላት ላይ ባጋጠመው የውሃ መቀነስ ሳቢያ በርካታ ሀገራትን የሚያካልለው የራይን ወንዝ ከሚሰጠው የባህር ትራንስፖርት በግማሽ መቀነሱም ነው የተገለጸው።
በሰርቪያ እና በስፔን የተከሰተው የወንዞች በከፍተኛ መጠን መድረቅ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የሰጠሙ መርከቦች፣ ግዙፍ አውዳሚ ቦምቦች እና ሌሎች ቁሶችን ለዕይታ እንዲጋለጡ ማድረጉን አልጀዚራ በዘገባው አመላክቷል፡፡
የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎችም ሙቀቱና ድርቁ ያስከተለው ቀውስ በሩሲያ ዩክሬን ግጭት ሳቢያ ከተከሰተው የሸቀጦች ዋጋ ንረትና እጥረት ጋር ተዳምሮ የሀገራቱን ፈተና ከባድ እንዳደረገው መግለጻቸውን ሺንዋ ዘግቧል።