ድንበር-ዘለል የጸጥታ እና የደህንነት ስጋቶችን መከላከል የሚያስችል ስልጠና እየተሰጠ ነው
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ድንበር-ዘለል የጸጥታ እና የደህንነት ስጋቶችን በብቃት ለመከላከል የሚያስችል ስልጠና ለኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኢንተለጀንስ አመራሮች እየተሰጠ ነው፡፡
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል÷ ስልጠናው መረጃ -መር የፖሊስ አገልግሎትን ለማሳደግ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው አብራርተዋል፡፡
የመረጃ ትንተና አቅምን የሚያጎለብት ስልጠና መዘጋጀቱ በስራ ላይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን ለመፍታት እና ክፍተቶችን ለመሙላት እንደሚያግዝም አንስተዋል፡፡
የኢንተለጀንስ መምሪያ የመፈፀም አቅሙን ለማጠናከር የፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅና ከሌሎች ተቋማት ጋር በመቀናጀት ስልጠና ሲሰጥ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡
በተጨማሪም ስልጠናው የሀገር ውስጥና ድንበር- ዘለል ወንጀሎችን ለመከላከልና የሽብር ወንጀሎችን በዘመናዊ መንገድ ለማስቆም እንደሚረዳ ነው የጠቆሙት፡፡
ስልጠናው የመረጃ ደህንነትና የስጋት ትንተና፣ የወንጀል ስጋቶች ላይ የሚኖሩ ለውጦችን በመገንዘብ የወንጀል መከላከልና ምርመራ ስራን ለማከናወን የሚያስችሉ ስትራቴጂዎች እንዲቀረጹ ለማድረግ እንደሚያግዝ መገለጹን ከፌደራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡