ምርጫ ቦርድ የፌዴሬሽን ም/ቤት አፈ-ጉባዔ ባቀረቡት የሕዝበ ውሣኔ ማደራጀት ጥያቄ ላይ ውሣኔ አሳለፈ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የዴሬሽን ምክር ቤት ላቀረበው የሕዝበ ውሣኔ ማደራጀት ጥያቄ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ የሚያስፈልገውን የጊዜ ታሳቢ ያደረገ የጊዜ ሰሌዳ እንደሚያሳውቅ ገለጸ፡፡
ቦርዱ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ÷ የፌደሬሽ ምክር ቤት በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት የሚገኙ 6 ዞኖች ማለትም የጋሞ፣ ወላይታ፣ ጎፋ፣ ጌዴኦ፣ ኮንሶ እና የደቡብ ኦሞ ዞኖች እንዲሁም 5 ልዩ ወረዳዎች ማለትም የቡርጂ፣ የአማሮ፣ የደራሼ፣ የባስኬቶ እና የአሌ ምክር ቤቶች አንድ የጋራ ክልል ለመመስረት ወስነው ጥያቄ ስላቀረቡ በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ ሕዝበ ውሳኔ በማደራጀት ውጤቱን ለምክር ቤቱ እንዲያቀርብ ለቦርዱ ማሳወቁን አንስቷል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም ጉዳዩን አግባብነት ካላቸው ህጎች አንፃር የተመለከተ መሆኑ በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡
በዚህም መሰረት ይህን ሕዝበ ውሳኔ ለማደራጀት እንደ ግብዓት ሆኖ ለቦርዱ ያገለግል ዘንድ ከላይ የተገለጹት ከስድስቱ ዞኖች እና የአምስቱ ልዩ ወረዳዎች በየራሳቸው ምክር ቤቶች ሕዝበ ውሳኔውን በጉዳዩ ላይ የሰጧቸውን ውሳኔዎች፣ ውሳኔያቸውን ለማስፈጸም ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ያቀረቧቸውን ጥያቄዎች፣ እንዲሁም አያይዘው ለምክር ቤቱ የላኳቸው ሌሎች ሰነዶች እንዲልኩለት ምክር ቤቱን ጠይቋል፡፡
በሌላ በኩል የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከላይ በተጠቀሱት 6 ዞኖች እና 5 ወረዳዎች ከሚደረገው የህዝብ ውሳኔ በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ እንዲደራጅ ለቦርዱ ቀን የቆረጠውን በተመለከተ ቦርዱ ጉዳዩን አግባብነት ካላቸው የህግ ማእቀፎች አንፃር በጥልቅ መመርመሩን አንስቷል፡፡
በሕገ ንግስቱ አንቀጽ 102 መሠረት በገለልተኛነት ከማንኛውም ተጽእኖ ነፃ የሆነ እውነተኛ ምርጫን ለማካሄድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በብቸኝነት የተቋቋመ ሕገ ንግስታዊ ተቋም መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በዚህ ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ፥ በሌሎች የምርጫ ህጎች እንዲሁም በዓለም አቀፍ በጎ አሰራሮች እንደተረጋገጠው ቦርዱ ይሀን የተቋቋመበትን አላማ ለማስፈፀም ከተቋማዊ እና መዋቅራዊ ነፃነት በተጨማሪ በህግ ተለይተው የተሰጡትን ስልጣን እና ሃላፊነቶች በተመለከተ የሚኖረው የውሳኔ እና የስራ አፈፃፀም በሁሉም መከበር እንደሚኖርበት አስገንዝቧል፡፡
በዚሁ አግባብ በቦርዱ ማቋቋሚያ ዋጅ ቁጥር 1133/2011 አንቀጽ 7 (22) አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተከናውኖ ምርጫዎች ወይም የህዝበ ውሳኔዎች ደረጃቸውን በጠበቀ ሁኔታ ለማካሔድ የሚወስደውን ጊዜ ምን ያህል እንደሆነ የመወሰን ብሎም በህግ በአጠቃላይ ሁኔታ ከተቀመጡት የጊዜ ገደቦች ሳይወጣ (ለምሳሌ የህገ መንግስት አንቀፅ 47(3) ለን ይመለከቷል) የሚካሄዱበትን መርሐ ግብር ሰሌዳ የማዘጋጀት፣ የማጽደቅና እንደ አስፈላጊነቱም የማሻሻልና የማስፈጸም ሥልጣን የተቋሙ ብቻ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በዚሁ መሰረት ቦርዱ ለዚህ ጉዳይ አፈፃፀም የሎጂስቲክስ ዝግጅት ለማድረግ፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች ምልመላ እና ምደባ ለመተግበር፣ የምርጫ ፀጥታ ጉዳይን ለመገምገም፣ የመራጮች ትምህርት ለመስጠት፣ የምርጫ ጣቢያዎች ለማደራጀት፣ ለታዛቢ ሲቪል ማህበራት ፈቃድ ለስጠት እና በጉዳዩ ላይ የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት ለማወያየት የሚያስፈልገውን ጊዜ ታሳቢ ያደረገ የጊዜ ሰሌዳ አውጥቶ ለምክር ቤቱ እንደሚገልፅ አስታውቋል፡፡